ትንቢተ ዘካርያስ

1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14


ምዕራፍ 7

በንጉሡም በዳርዮስ በአራተኛው ዓመት ካሴሉ በሚባል በዘጠነኛው ወር በአራተኛው ቀን የእግዚአብሔር ቃል ወደ ዘካርያስ መጣ።
2 ፤ የቤቴልም ሰዎች ሳራሳርንና ሬጌሜሌክን ሰዎቻቸውንም በእግዚአብሔር ፊት ይለምኑ ዘንድ፥
3 ፤ ለሠራዊት ጌታ ለእግዚአብሔር ቤት ካህናት ለነቢያትም። ባለፉት ዓመታት እንዳደረግሁት በአምስተኛው ወር መለየትና ማልቀስ ይገባኛልን? ብለው ይናገሩ ዘንድ ልኮአቸው ነበር።
4 ፤ የሠራዊትም ጌታ የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ።
5 ፤ ለምድሩ ሕዝብ ሁሉ ለካህናትም እንዲህ ብለህ ተናገራቸው። በዚህ በሰባው ዓመት በአምስተኛውና በሰባተኛው ወር በጾማችሁና ባለቀሳችሁ ጊዜ፥ በውኑ ለእኔ ጾም ጾማችሁልኝ?
6 ፤ በምትበሉበትና በምትጠጡበትስ ጊዜ፥ ለራሳችሁ የምትበሉና የምትጠጡ አይደላችሁምን?
7 ፤ ኢየሩሳሌምና በዙሪያዋ ያሉ ከተሞች ገና ሰዎች ባሉባቸው ጊዜ፥ በምቾትም ተቀምጠው ሳሉ፥ ደቡቡና ቈላውም ሰዎች ባሉባቸው ጊዜ፥ እግዚአብሔር በቀደሙት ነቢያት እጅ የተናገረውን ቃል መስማት አይገባችሁምን?
8 ፤ የእግዚአብሔርም ቃል ወደ ዘካርያስ እንዲህ ሲል መጣ።
9 ፤ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ብሎ ተናግሮአል። እውነተኛውን ፍርድ ፍረዱ፤ ቸርነትንና ምሕረትን ሁላችሁ ለወንድሞቻችሁ አድርጉ፤
10 ፤ መበለቲቱንና ድሀ አደጉን፥ መጻተኛውንና ችግረኛውን አትበድሉ፤ ከእናንተም ማንም በወንድሙ ላይ ክፉውን ነገር በልቡ አያስብ።
11 ፤ እነርሱ ግን ደንደሳቸውን አዞሩ እንጂ መስማትን እምቢ አሉ፤ እንዳይሰሙም ጆሮአቸውን አደነቈሩ።
12 ፤ የሠራዊትም ጌታ እግዚአብሔር በቀደሙት ነቢያት እጅ በመንፈሱ የላከውን ሕጉንና ቃሉን እንዳይሰሙ ልባቸውን እንደ አልማዝ አጠነከሩ፤ ስለዚህ ከሠራዊት ጌታ ከእግዚአብሔር ዘንድ ታላቅ ቍጣ መጣ።
13 ፤ እኔ በጠራሁ ጊዜ እነርሱ እንዳልሰሙኝ፥ እንዲሁ እነርሱ በሚጠሩበት ጊዜ እኔ አልሰማም፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፤
14 ፤ ወደማያውቁአቸውም አሕዛብ ሁሉ በዐውሎ ነፋስ በተንኋቸው። እንዲሁ ከእነርሱ በኋላ ምድሪቱ ባድማ ሆናለች፥ የሚተላለፍባትና የሚመላለስባትም አልነበረም፤ ያማረችውንም ምድር ባድማ አደረጉአት።