ምዕራፍ 26

የይሁዳም ሕዝብ ሁሉ የአሥራ ስድስት ዓመት ጕልማሳ የነበረውን ዖዝያንን ወስደው በአባቱ በአሜስያስ ፋንታ አነገሡት።
2 ፤ ንጉሡም ከአባቶቹ ጋር ከአንቀላፋ በኋላ ዖዝያን ኤላትን ሠራ፥ ወደ ይሁዳም መለሳት።
3 ፤ ዖዝያንም መንገሥ በጀመረ ጊዜ የአሥራ ስድስት ዓመት ጕልማሳ ነበረ፥ በኢየሩሳሌምም አምሳ ሁለት ዓመት ነገሠ፤ እናቱም ይኮልያ የተባለች የኢየሩሳሌም ሴት ነበረች።
4 ፤ አባቱም አሜስያስ እንዳደረገው ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ቅን ነገር አደረገ።
5 ፤ እግዚአብሔርንም መፍራት ባስተማረ በዘካርያስ ዘመን እግዚአብሔርን ይፈልግ ዘንድ ልብ አደረገ፤ እግዚአብሔርንም በፈለገ ጊዜ እግዚአብሔር ነገሩን አከናወነለት።
6 ፤ ወጥቶም ከፍልስጥኤማውያን ጋር ተዋጋ፥ የጌትንና የየብናን የአዞጦንንም ቅጥር አፈረሰ፤ በአዛጦንና በፍልስጥኤማውያንም አገር ከተሞችን ሠራ።
7 ፤ እግዚአብሔርም በፍልስጥኤማውያንና በጉርበኣል በሚኖሩ ዓረባውያን በምዑናውያንም ላይ ረዳው።
8 ፤ አሞናውያንም ለዖዝያን ገበሩ፤ እጅግም በርትቶ ነበርና ዝናው እስከ ግብጽ መግቢያ ድረስ ተሰማ።
9 ፤ ዖዝያንም በኢየሩሳሌም በማዕዘኑ በርና በሸለቆው በር ቅጥሩም በዞረበት ማዕዘን አጠገብ ግንቦችን ሠርቶ መሸጋቸው።
10 ፤ ብዙም እንስሶች ነበሩበትና በምድረ በዳና በቈላው በደጋውም ግንብ ሠራ፥ ብዙ ጕድጓድም ማሰ፤ ደግሞም እርሻ ይወድድ ነበርና በተራራማውና በፍሬያማው ስፍራ አራሾችና አትክልተኞች ነበሩት።
11 ፤ ደግሞም ለዖዝያን በሠራዊት ውስጥ ሰልፈኞች ነበሩት፤ በንጉሡ አለቃ በሐናንያ ትእዛዝ በአለቃው በመዕሤያና በጸሐፊው በይዒኤል እጅ እንደ ተቈጠሩ ወደ ሰልፍ በየቍጥራቸው ይወጡ ነበር።
12 ፤ የአባቶቻቸውም ቤቶች አለቆች የጽኑዓን ኃያላኑ ቍጥር ሁሉ ሁለት ሺህ ስድስት መቶ ነበረ።
13 ፤ ንጉሡንም በጠላቱ ላይ ያግዝ ዘንድ፥ በታላቅ ኃይል ወደ ሰልፍ የሚወጣ፥ ከእጃቸው በታች የነበረ ሠራዊት ሦስት መቶ ሰባት ሺህ አምስት መቶ ነበረ።
14 ፤ ዖዝያንም ለጭፍራው ሁሉ ጋሻና ጦር፥ ራስ ቍርና ጥሩር፥ ቀስትና የሚወነጭፉትን ድንጋይ አዘጋጀላቸው።
15 ፤ በኢየሩሳሌምም በብልሃተኞች እጅ የተሠሩትን፥ በግንብና በቅጥር ላይ የሚኖሩትን፥ ፍላጻና መርግ የሚወረወርባቸውን መሣሪያዎች አደረገ፤ እስኪበረታም ድረስ እግዚአብሔር በድንቅ ረድቶታልና ዝናው እስከ ሩቅ ድረስ ተሰማ።
16 ፤ ነገር ግን በበረታ ጊዜ ለጥፋት ልቡ ታበየ፥ አምላኩንም እግዚአብሔርን በደለ፤ ወደ መቅደስ ገብቶ በዕጣን መሠዊያ ላይ ዐጠነ።
17 ፤ ካህኑም ዓዛርያስ ከእርሱም ጋር ጽኑዓን የነበሩ ሰማንያ የእግዚአብሔር ካህናት ተከትለው ገቡ።
18 ፤ ንጉሡንም ዖዝያንን እየተቃወሙ። ዖዝያን ሆይ፥ ዕጣን ማጠን የተቀደሱት የአሮን ልጆች የካህናቱ ሹመት ነው እንጂ ለእግዚአብሔር ታጥን ዘንድ ለአንተ አይገባህም፤ በድለሃልና ከመቅደሱ ውጣ፤ ከአምላክህም ከእግዚአብሔር ዘንድ ክብር አይሆንልህም አሉት።
19 ፤ ዖዝያንም ተቈጣ፤ የሚያጥንበትም ጥና በእጁ ነበረ፤ ካህናቱንም በተቈጣ ጊዜ በካህናቱ ፊት በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ በዕጣኑ መሠዊያ አጠገብ ሳለ በግምባሩ ላይ ለምጽ ታየ።
20 ፤ ታላቁም ካህን ዓዛርያስ ካህናቱም ሁሉ ተመለከቱት፥ እነሆም፥ በግምባሩ ላይ ለምጽ ነበረ፤ ፈጥነውም አባርረሩት፥ እርሱም ደግሞ እግዚአብሔር ቀሥፎት ነበርና ይወጣ ዘንድ ቸኰለ።
21 ፤ ንጉሡም ዖዝያን እስኪሞት ድረስ ለምጻም ነበረ፤ ለምጻምም ሆኖ ከእግዚአብሔር ቤት ተቈርጦአልና በተለየ ቤት ይቀመጥ ነበር፤ ልጁም ኢዮአታም በንጉሡ ቤት ላይ ሆኖ በምድሩ ሕዝብ ላይ ይፈርድ ነበር።
22 ፤ የቀረውንም የፊተኛውንና የኋለኛውን የዖዝያንን ነገር ነቢዩ የአሞጽ ልጅ ኢሳይያስ ጽፎታል።
23 ፤ ዖዝያንም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፥ ለምጻም ነው ብለውም ከአባቶቹ ጋር በነገሥታቱ መቃብር እርሻ ውስጥ ቀበሩት፤ ልጁም ኢዮአታም በእርሱ ፋንታ ነገሠ።