መጽሐፈ ዜና መዋዕል ካልዕ።
ምዕራፍ 16
አሳ በነገሠ በሠላሳ ስድስተኛው ዓመት የእስራኤል ንጉሥ ባኦስ በይሁዳ ላይ ወጣ፥ ወደ ይሁዳም ንጉሥ ወደ አሳ ማንም መውጣትና መግባት እንዳይችል ራማን ሠራ።
2 ፤ አሳም ከእግዚአብሔር ቤትና ከንጉሡ ቤት መዝገብ ብርና ወርቅ ወስዶ።
3 ፤ በአባቴና በአባትህ መካከል እንደ ነበረው ቃል ኪዳን በእኔና በአንተ መካከል ይሆናል፤ እነሆ ብርና ወርቅ ሰድጄልሃለሁ፤ እርሱ ከእኔ ዘንድ እንዲርቅ ሄደህ ከእስራኤል ንጉሥ ከባኦስ ጋር ያለህን ቃል ኪዳን አፍርስ ብሎ በደማስቆ ወደተቀመጠው ወደ ሶሪያ ንጉሥ ወደ ወልደ አዴር ሰደደ።
4 ፤ ወልደ አዴር ንጉሡን አሳን እሺ አለው፥ የሠራዊቱም አለቆች በእስራኤል ከተሞች ላይ ሰደደ፤ እነርሱም ዒዮንንና ዳንን አቤልማይምንና የንፍታሌምን የዕቃ ቤት ከተሞች ሁሉ መቱ።
5 ፤ ባኦስም በሰማ ጊዜ ራማን መሥራት ተወ፥ ሥራውንም አቋረጠ።
6 ፤ ንጉሡም አሳ የይሁዳን ሰዎች ሁሉ ሰበሰበ፤ ባኦስ ይሠራበት የነበረውን የራማን ድንጋይና እንጨት አስወገዱ፥ እርሱም ጌባንና ምጽጳን ሠራበት።
7 ፤ በዚያን ጊዜም ባለ ራእዩ አናኒ ወደ ይሁዳ ንጉሥ ወደ አሳ መጥቶ እንዲህ አለው። በሶሪያ ንጉሥ ታምነሃልና፥ በአምላክህም በእግዚአብሔር አልታመንህምና ስለዚህ የሶሪያ ንጉሥ ጭፍራ ከእጅህ አምልጦአል።
8 ፤ ኢትዮጵያውያንና የልብያ ሰዎች እጅግ ብዙ ሰረገሎችና ፈረሰኞች የነበሩአቸው እጅግ ታላቅ ጭፍራ አልነበሩምን? በእግዚአብሔር ስለ ታመንህ በእጅህ አሳልፎ ሰጣቸው፥
9 ፤ እግዚአብሔር ልቡ በእርሱ ዘንድ ፍጹም የሆነውን ያጸና ዘንድ ዓይኖቹ በምድር ሁሉ ይመለከታሉና። አሁንም ስንፍና አድርገሃል። ስለዚህም ከዛሬ ጀምሮ ሰልፍ ይሆንብሃል።
10 ፤ አሳም በባለ ራእዩ ላይ ተቈጣ፤ ስለዚህም ነገር ተቈጥቶአልና በግዞት አኖረው፤ በዚያን ጊዜም አሳ ከሕዝቡ አያሌ ሰዎችን አስጨነቀ።
11 ፤ የአሳም የፊተኛውና የኋለኛው ነገር፥ እነሆ፥ በይሁዳና በእስራኤል ነገሥታት መጽሐፍ ተጽፎአል።
12 ፤ በነገሠም በሠላሳ ዘጠኝኛው ዓመት አሳ እግሩን ታመመ፤ ደዌውም ጸናበት፤ ነገር ግን በታመመ ጊዜ ባለ መድኃኒቶችን እንጂ እግዚአብሔርን አልፈለገም።
13 ፤ አሳም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፥ በነገሠም በአርባ አንደኛው ዓመት ሞተ።
14 ፤ ለእርሱም ለራሱ በሠራው መቃብር በዳዊት ከተማ ቀበሩት፤ በቀማሚ ብልሃት የተሰናዳ ልዩ ልዩ መልካም ሽቱ በተሞላ አልጋ ላይም አኖሩት፤ እጅግም ታላቅ የሆነ የመቃብር ወግ አደረጉለት።