ምዕራፍ 1

የዳዊት ልጅ ሰሎሞን በመንግሥቱ በረታ፤ አምላኩም እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ነበረ፥ እጅግም አገነነው።
2 ፤ ሰሎሞንም ለእስራኤል ሁሉ፥ ለሻለቆች፥ ለመቶ አለቆችም፥ ለፈራጆችም፥ በእስራኤልም ሁሉ ዘንድ ለነበሩ መሳፍንት ሁሉ፥ ለአባቶች ቤቶች አለቆች ተናገረ።
3 ፤ ሰሎሞንም ከእርሱም ጋር ጉባኤው ሁሉ የእግዚአብሔር ባሪያ ሙሴ በምድረ በዳ የሠራው የእግዚአብሔር መገናኛ ድንኳን በዚያ ነበረና በገባዖን ወዳለው የኮረብታ መስገጃ ሄዱ።
4 ፤ ለእግዚአብሔር ታቦት ግን ዳዊት በኢየሩሳሌም ድንኳን ተክሎለት ነበርና ዳዊት ከቂርያትይዓሪም ወዳዘጋጀለት ስፍራ አምጥቶት ነበር።
5 ፤ የሆርም ልጅ የኡሪ ልጅ ባስልኤል የሠራው የናስ መሠዊያ በዚያ በእግዚአብሔር ማደሪያ ፊት ነበረ፤ ሰሎሞንም ጉባኤውም ይህን ይፈልጉት ነበር።
6 ፤ ሰሎሞንም በእግዚአብሔር ፊት በመገናኛው ድንኳን አጠገብ ወዳለው ወደ ናሱ መሠዊያ ወጣ፥ በዚያም አንድ ሺህ የሚቃጠል መሥዋዕት አቀረበ።
7 ፤ በዚያም ሌሊት እግዚአብሔር። ምን እንድሰጥህ ለምነኝ ሲል ለሰሎሞን ተገለጠ።
8 ፤ ሰሎሞንም እግዚአብሔርን አለው። ከአባቴ ከዳዊት ጋር ታላቅ ምሕረት አድርገሃል፥ በእርሱም ፋንታ አንግሠኸኛል።
9 ፤ አሁንም፥ አቤቱ አምላክ ሆይ፥ ቍጥሩ እንደ ምድር ትቢያ በሆነው በብዙ ሕዝብ ላይ አንግሠኸኛልና ለአባቴ ለዳዊት የሰጠኸው ተስፋ ይጽና።
10 ፤ አሁንም በዚህ ሕዝብ ፊት እወጣና እገባ ዘንድ ጥበብንና እውቀትን ስጠኝ፤ ይህን በሚያህል በዚህ በታላቅ ሕዝብ ላይ ይፈርድ ዘንድ የሚችል የለምና።
11 ፤ እግዚአብሔርም ሰሎሞንን። ይህ በልብህ ነበረና፥ ባለጠግነትንና ሀብትን ክብርንና የጠላቶችህን ነፍስ ረጅምም ዕድሜን አልለመንህምና፥ ነገር ግን ባነገሥሁህ በሕዝቤ ላይ ለመፍረድ ትችል ዘንድ ጥበብንና እውቀትን ለራስህ ለምነሃልና ጥበብንና እውቀትን ሰጥቼሃለሁ፤
12 ፤ ከአንተ በፊትም ከነበሩት ከአንተም በኋላ ከሚነሡት ነገሥታት አንድ ስንኳ የሚመስልህ እንዳይኖር ባለጠግነትንና ሀብትን ክብርንም እሰጥሃለሁ አለው።
13 ፤ ሰሎሞንም በገባዖን ካለው ከኮረብታው መስገጃ ከመገናኛው ድንኳን ወደ ኢየሩሳሌም መጣ፤ በእስራኤልም ላይ ነገሠ።
14 ፤ ሰሎሞንም ሰረገሎቹንና ፈረሰኞችን ሰበሰበ፥ አንድ ሺህም አራት መቶ ሰረገሎች፥ አሥራ ሁለት ሺህም ፈረሰኞች ነበሩት፤ በሰረገሎች ከተሞችና ከእርሱ ጋር በኢየሩሳሌም አኖራቸው።
15 ፤ ንጉሡም ብሩንና ወርቁን በኢየሩሳሌም እንደ ድንጋይ እንዲበዛ አደረገው፤ የዝግባም እንጨት ብዛት በቈላ እንደሚበቅል ሾላ ሆነ።
16 ፤ ሰሎሞንም ፈረሶችን ከግብጽና ከቀዌ አስመጣ፤ የንጉሡም ነጋዴዎች በገንዘብ እየገዙ ከቀዌ ያመጡአቸው ነበር።
17 ፤ አንዱም ሰረገላ በስድስት መቶ፥ አንዱም ፈረስ በመቶ አምሳ ሰቅል ብር ከግብጽ ይወጣ ነበር፤ እንዲሁም ለኬጢያውያንና ለሶሪያ ነገሥታት ሁሉ በእጃቸው ያመጡላቸው ነበር።