መጽሐፈ ዜና መዋዕል ካልዕ።
ምዕራፍ 15
የእግዚአብሔርም መንፈስ በዖዴድ ልጅ በዓዛርያስ ላይ ሆነ፤
2 ፤ አሳንም ሊገናኘው ወጣ፥ እንዲህም አለው። አሳ ይሁዳና ብንያም ሁሉ ሆይ፥ ስሙኝ፤ እናንተ ከእግዚአብሔር ጋር ስትሆኑ እርሱ ከእናንተ ጋር ነው፤ ብትፈልጉትም ይገኝላችኋል፤ ብትተዉት ግን ይተዋችኋል።
3 ፤ እስራኤልም ብዙ ዘመን ያለ እውነተኛ አምላክ፥ ያለ አስተማሪም ካህን፥ ያለ ሕግም ይኖሩ ነበር።
4 ፤ በመከራቸውም ወደ እስራኤል አምላክ ወደ እግዚአብሔር ተመልሰው በፈለጉት ጊዜ አገኙት።
5 ፤ በዚያም ዘመን ለሚወጣውና ለሚገባው ሰላም አልነበረም፥ በምድርም በሚኖሩት ሁሉ ላይ ታላቅ ድንጋጤ ነበረ።
6 ፤ እግዚአብሔር በመከራው ሁሉ ያስጨንቃቸው ነበርና ወገን ከወገን ጋር፥ ከተማም ከከተማ ጋር ይዋጋ ነበር።
7 ፤ እናንተ ግን ለሥራችሁ ብድራት ይሆንላችኋልና በርቱ፥ እጃችሁም አይላላ።
8 ፤ አሳም ይህን ቃልና የነቢዩን የዖዴድን ትንቢት በሰማ ጊዜ ልቡ ጸና፥ ከይሁዳና ከቢንያምም አገር ሁሉ በተራራማውም በኤፍሬም አገር ከያዛቸው ከተሞች ጸያፉን ነገር አስወገደ፤ በእግዚአብሔርም ቤት ፊት የነበረውን የእግዚአብሔርን መሠዊያ አደሰ።
9 ፤ አምላኩም እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር እንደ ሆነ ባዩ ጊዜ ከእስራኤል ዘንድ ብዙ ሰዎች ወደ እርሱ ተጠግተው ነበርና እርሱ ይሁዳንና ብንያምን ሁሉ፥ ከኤፍሬምና ከምናሴም ከስምዖንም መጥተው ከእነርሱ ጋር የተቀመጡትን ሰበሰበ።
10 ፤ አሳም በነገሠ በአሥራ አምስተኛው ዓመት በሦስተኛው ወር በኢየሩሳሌም ተሰበሰቡ።
11 ፤ በዚያም ቀን ካመጡት ምርኮ ሰባት መቶ በሬዎችና ሰባት ሺህ በጎች ለእግዚአብሔር ሠዉ።
12 ፤ በፍጹም ልባቸውና በፍጹም ነፍሳቸው የአባቶቻቸውን አምላክ እግዚአብሔርን ይሹ ዘንድ ቃል ኪዳን አደረጉ፤
13 ፤ የእስራኤልንም አምላክ እግዚአብሔርን የማይፈልግ፥ ታናሽ ወይም ታላቅ፥ ወንድ ወይም ሴት ቢሆን፥ ይገደል ዘንድ ማሉ።
14 ፤ ለእግዚአብሔርም በታላቅ ድምፅና በእልልታ፥ በእምቢልታና በቀንደ መለከት ማሉ።
15 ፤ በፍጹምም ልባቸው ምለዋልና፥በፍጹምም ሕሊናቸው ፈልገውታልና፥ እርሱም ተገኝቶላቸዋልና ይሁዳ ሁሉ በመሐላው ደስ አላቸው፤ እግዚአብሔርም በዙሪያቸው ዕረፍት ሰጣቸው።
16 ፤ ንጉሡም አሳ እናቱን መዓካን በማምለኪያ ዐፀድ ጣዖት ስላደረገች ከእቴጌነትዋ አዋረዳት፤ አሳም ምስልዋን ቈርጦ ቀጠቀጠው፥ በቄድሮንም ወንዝ አጠገብ አቃጠለው።
17 ፤ በኮረብታ ላይ የነበሩትን መስገጃዎች ግን ከእስራኤል አላራቀም፤ ይሁን እንጂ የአሳ ልብ በዘመኑ ሁሉ ፍጹም ነበረ።
18 ፤ አባቱም የቀደሰውን፥ እርሱም የቀደሰውን ወርቁንና ብሩን፥ ልዩ ልዩውንም ዕቃ ወደ እግዚአብሔር ቤት አገባ።
19 ፤ አሳም እስከ ነገሠበት እስከ ሠላሳ አምስተኛው ዓመት ድረስ ሰልፍ አልነበረም።