ኦሪት ዘዳግም
ምዕራፍ 33
የእግዚአብሔር ሰው ሙሴ ሳይሞት የእስራኤልን ልጆች የባረከባት በረከት ይህች ናት።
2 ፤ እንዲህም አለ።  እግዚአብሔር ከሲና መጣ፥  በሴይርም ተገለጠ፤  ከፋራን ተራራ አበራላቸው፥  ከአእላፋትም ቅዱሳኑ መጣ፤  በስተ ቀኙም የእሳት ሕግ ነበረላቸው።
3 ፤ ሕዝቡንም ወደዳቸው፤  ቅዱሳኑ ሁሉ በእጅህ ናቸው፤  በእግሮችህም አጠገብ ተቀመጡ፤  ቃሎችህን ይቀበላሉ።
4 ፤ ሙሴ ለያዕቆብ ጉባኤ ርስት የሆነውን  ሕግ አዘዘን።
5 ፤ የሕዝቡ አለቆች ከእስራኤል ነገዶች  ሁሉ ጋር በተከማቹ ጊዜ፥  ንጉሥ በይሹሩን ነበረ።
6 ፤ ሮቤል በህይወት ይኑር፥ አይሙት፤  ሰዎቹም በቍጥር ብዙ ይሁኑ።
7 ፤ የይሁዳ በረከት ይህ ነው፤ እንዲህም አለ።  አቤቱ፥ የይሁዳን ድምፅ ስማ፥  ወደ ወገኖቹም አግባው፤  እጆቹ ይጠንክሩለት፤  በጠላቶቹ ላይ ረዳት ትሆነዋለህ።
8 ፤ ስለ ሌዊም እንዲህ አለ፥  ቱሚምህና ኡሪምህ ለቅዱስህ ሰው ነው፥  በማሳህ ለፈተንኸው፥  በመሪባ ውኃም ለተከራከርኸው፤
9 ፤ ስለ አባቱና ስለ እናቱ። አላየሁም ላለ፥  ወንድሞቹንም ላላስተዋለ፥  ልጆቹንም ላላወቀ፤  ቃልህን አደረጉ፥  ቃል ኪዳንህንም ጠበቁ።  
10 ፤ ፍርድህን ለያዕቆብ፥  ሕግህንም ለእስራኤል ያስተምራሉ፤  በፊትህ ዕጣንን፥  በመሠዊያህም የሚቃጠል መሥዋዕት ይሠዋሉ።  
11 ፤ አቤቱ፥ ሀብቱን ባርክ፥  የእጁንም ሥራ ተቀበል፤  የሚነሣበትን ወገብ ውጋው፥  የሚጠሉትም አይነሡ።
12 ፤ ስለ ብንያምም እንዲህ አለ።  በእግዚአብሔር የተወደደ በእርሱ  ዘንድ ተማምኖ ይኖራል፤  ቀኑን ሁሉ ይጋርደዋል፥  በትከሻውም መካከል ያድራል።
13 ፤ ስለ ዮሴፍም እንዲህ አለ፥  ምድሩ ከእግዚአብሔር ዘንድ የተባረከ ይሁን፤  በሰማያት ገናንነት በጠል፥  በታችኛውም ቀላይ፥  
14 ፤ በፀሐዩ ፍሬያት ገናንነት፥  በጨረቃውም መውጣት ገናንነት  
15 ፤ በቀደሙትም ተራሮች ከፍተኛነት፥  በዘላለሙም ኮረብቶች ገናንነት፥  
16 ፤ በምድሪቱም ገናንነትና ሞላዋ፥  በቍጥቋጦው ውስጥ ከነበረው በረከት  በዮሴፍ ራስ ላይ፥ ከወንድሞቹም በተለየው ራስ አናት ላይ ይውረድ።  
17 ፤ ለላሞች በኵር ግርማ ይሆናል፤  ቀንዶቹ አንድ ቀንድ እንዳለው ናቸው፤  በእነርሱ እስከ ምድር ዳርቻ ያሉትን  አሕዛብ ሁሉ ይወጋል፤  የኤፍሬም እልፍ አእላፋት፥  የምናሴም አእላፋት እነርሱ ናቸው።
18 ፤ ስለ ዛብሎንም እንዲህ አለ። ዛብሎን ሆይ፥ በመውጣትህ፥  ይሳኮር ሆይ፥ በድንኳንህ ውስጥ ደስ ይበላችሁ።  
19 ፤ የተሰወረውን የአሸዋውን መዝገብ፥  የባሕሩንም ባለጠግነት ይጠባሉና  አሕዛብን ወደ ተራራው ይጠራሉ፤  በዚያ የጽድቅ መሥዋዕት ይሠዋሉ።
20 ፤ ስለ ጋድም እንዲህ አለ።  ጋድን ሰፊ ያደረገ ቡሩክ ይሁን፤  እንደ አንበሳይቱ ዐርፎአል፤  ክንድንና ራስን ይቀጠቅጣል።  
21 ፤ በዚያ የአለቃ እድል ፈንታ ቀርቶአልና  የመጀመሪያውን ክፍል ለራሱ መረጠ፤  ወደ ሕዝብ አለቆችም መጣ፤  የእግዚአብሔርንም ጽድቅ፥  ፍርዱንም ከእስራኤል ጋር አደረገ።
22 ፤ ስለ ዳንም እንዲህ አለ።  ዳን የአንበሳ ደቦል ነው፤  ከባሳን ዘልሎ ይወጣል።
23 ፤ ስለ ንፍታሌምም እንዲህ አለ።  ንፍታሌም በሞገስ ጠግቦአል፥  የእግዚአብሔርንም በረከት ተሞልቶአል፤  ባሕሩንና ደቡቡን ይወርሳል።
24 ፤ ስለ አሴርም እንዲህ አለ።  አሴር በልጆች የተባረከ ይሁን፤  በወንድሞቹ የተወደደ ይሁን፤ እግሩንም በዘይት ውስጥ ያጥልቅ።  
25 ፤ ጫማህ ብረትና ናስ ይሆናል፤  እንደ ዕድሜህ እንዲሁ ኃይልህ ይሆናል።  
26 ፤ ይሹሩን ሆይ፥ በሰማያት ላይ ለረድኤትህ፥  በደመናትም ላይ በታላቅነት እንደሚሄድ  እንደ እግዚአብሔር ያለ ማንም የለም።  
27 ፤ መኖሪያህ የዘላለም አምላክ ነው፥  የዘላለምም ክንዶች ከአንተ በታች ናቸው፤  ጠላትህን ከፊትህ አውጥቶ።  አጥፋው ይላል።  
28 ፤ እስራኤልም ተማምኖ፥  የያዕቆብም ምንጭ ብቻውን፥  እህልና የወይን ጠጅ ባለባት ምድር ይኖራል፤  ሰማያቱም ጠልን ያንጠባጥባሉ።  
29 ፤ እስራኤል ሆይ፥ ምስጉን ነህ፤  በእግዚአብሔር የዳነ ሕዝብ እንደ አንተ ማን ነው?  እርሱ የረድኤትህ ጋሻ፥  የከፍተኛነትህም ሰይፍ ነው።  ጠላቶችህም ይገዙልሃል፤  አንተም ከፍታቸውን ትረግጣለህ።