ምዕራፍ 31

ሙሴም ሄዶ ይህንን ቃል ለእስራኤል ሁሉ ነገረ።
2 ፤ አላቸውም። እኔ ዛሬ መቶ ሀያ ዓመት ሆኖኛል፤ ከዚህ በኋላ እወጣና እገባ ዘንድ አልችልም፤ እግዚአብሔርም። ይህን ዮርዳኖስን አትሻገርም ብሎኛል።
3 ፤ አምላክህ እግዚአብሔር እርሱ በፊትህ ያልፋል፤ እርሱ እነዚህን አሕዛብ ከፊትህ ያጠፋቸዋል ትወርሳቸውማለህ፤ እግዚአብሔርም እንደ ተናገረ ኢያሱ በፊትህ ይሻገራል።
4 ፤ እግዚአብሔርም ባጠፋቸው በአሞራውያን ነገሥታት በሴዎንና በዐግ በምድራቸውም እንዳደረገ ያደርግባቸዋል።
5 ፤ እግዚአብሔርም በፊታችሁ አሳልፎ ይጥላቸዋል፥ እንዳዘዝኋችሁም ትእዛዝ ሁሉ ታደርጉባቸዋላችሁ።
6 ፤ ጽኑ፥ አይዞአችሁ፥ አትፍሩ፥ ከፊታቸውም አትደንግጡ፤ አምላክህ እግዚአብሔር እርሱ ከአንተ ጋር ይሄዳል፤ አይጥልህም፥ አይተውህም።
7 ፤ ሙሴም ኢያሱን ጠርቶ በእስራኤል ሁሉ ፊት። አንተ ከዚህ ሕዝብ ጋር እግዚአብሔር ለአባቶቻቸው እንዲሰጥ ወደ ማለላቸው ምድር ትገባለህና፥ እርስዋንም ለእነርሱ ታወርሳለህና ጽና፥ አይዞህ።
8 ፤ በፊትህም የሚሄድ እርሱ እግዚአብሔር ነው፤ ከአንተ ጋር ይሆናል፥ አይጥልህም፥ አይተውህም፤ አትፍራ፥ አትደንግጥ አለው።
9 ፤ ሙሴም ይህችን ሕግ ጻፈ፥ የእግዚአብሔርንም የቃል ኪዳኑን ታቦት ይሸከሙ ለነበሩት ለሌዊ ልጆች ለካህናቱ ለእስራኤልም ሽማግሌዎች ሁሉ ሰጣት።
10 ፤ ሙሴም እንዲህ ብሎ አዘዛቸው። በሰባተኛው ዓመት መጨረሻ፥ በዕዳ ምሕረት ዘመን፥ በዳስ በዓል፥
11 ፤ እስራኤል ሁሉ በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት ይታይ ዘንድ እርሱ በመረጠው ስፍራ ሲከማች፥ ይህን ሕግ በእስራኤል ሁሉ ፊት በጆሮው አንብበው።
12 ፤ ይሰሙና ይማሩ ዘንድ፥ አምላካችሁንም እግዚአብሔርን ይፈሩ ዘንድ፥ የዚህንም ሕግ ቃሎች ሁሉ ጠብቀው ያደርጉ ዘንድ ሕዝቡን ወንዶችንና ሴቶችን ሕፃናቶችንም በአገራችሁ ደጅ ያለውንም መጻተኛ ሰብስብ።
13 ፤ የሕግ ቃላት የማያውቁ ልጆቻቸውም ዮርዳኖስን ተሻግራችሁ ልትወርሱአት በምትሄዱባት ምድር በምትኖሩበት ዘመን ሁሉ ይስሙ፥ አምላካችሁን እግዚአብሔርንም መፍራት ይማሩ።
14 ፤ እግዚአብሔርም ሙሴን። የምትሞትበት ቀን፥ እነሆ፥ ቀረበ፤ ኢያሱን ጠርተህ እርሱን አዝዘው ዘንድ በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ከእርሱ ጋር ቁም አለው። ሙሴና ኢያሱም ሄደው በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ቆሙ።
15 ፤ እግዚአብሔርም በድንኳኑ ውስጥ በደመና ዓምድ ተገለጠ፤ የደመናውም ዓምድ በድንኳኑ ደጃፍ ላይ ቆመ።
16 ፤ እግዚአብሔርም ሙሴን አለው። እነሆ፥ ከአባቶችህ ጋር ትተኛለህ፤ ይህም ሕዝብ ይነሣል፥ ይቀመጥባትም ዘንድ በሚሄድባት ምድር መካከል ያሉትን ሌሎችን አማልክት ተከትሎ ያመነዝራል፥ እኔንም ይተወኛል፥ ከእነርሱም ጋር ያደረግሁትን ቃል ኪዳን ያፈርሳሉ።
17 ፤ በዚያም ቀን ቍጣዬ ይነድድባቸዋል፥ እተዋቸውማለሁ፥ ፊቴንም እሰውርባቸዋለሁ፥ ለአሕዛብ መብል ይሆናሉ፤ በዚያም ቀን። በእውነት እግዚአብሔር በእኛ መካከል የለምና ይህ ክፉ ነገር ሁሉ አገኘን እስኪሉ ድረስ ብዙ ክፉ ነገርና ጭንቀት ይደርስባቸዋል።
18 ፤ ሌሎችን አማልክት ተከትለዋልና ስላደረጉት ክፋት ሁሉ እኔ በዚያ ቀን ፈጽሜ ፊቴን እሰውራለሁ።
19 ፤ አሁንም ይህችን መዝሙር ለእናንተ ጻፉ፥ ለእስራኤልም ልጆች አስተምሩአቸው፤ ይህችም መዝሙር በእስራኤል ላይ ምስክር ትሆንልኝ ዘንድ በአፋቸው አድርጓት።
20 ፤ ለአባቶቻቸው ወደ ማልሁላቸው፥ ወተትና ማር ወደ ምታፈስሰው ምድር ካገባኋቸው በኋላ፥ ከበሉም ከጠገቡም ከደነደኑም በኋላ፥ ሌሎችን አማልክት ተከትለው ያመልካሉ፥ እኔንም ይንቃሉ፥ ቃል ኪዳኔንም ያፈርሳሉ።
21 ፤ ዛሬ ወደ ማልሁላቸው ምድር ገና ሳላገባቸው የሚያስቡትን አሳብ አውቃለሁና፥ ከልጆቻቸውም አፍ አትረሳምና ብዙ ክፉ ነገርና ጭንቀት በደረሰባቸው ጊዜ ይህች መዝሙር ምስክር ሆና በፊታቸው ትመሰክራለች።
22 ፤ ሙሴም በዚያ ቀን ይህችን መዝሙር ጻፈ፥ ለእስራኤልም ልጆች አስተማራት።
23 ፤ የነዌንም ልጅ ኢያሱን። የእስራኤልን ልጆች ወደ ማልሁላቸው ምድር ታገባለህና ጽና፥ አይዞህ፤ እኔም ከአንተ ጋር እሆናለሁ ብሎ አዘዘው።
24 ፤ እንዲህም ሆነ፤ ሙሴ የዚህን ሕግ ቃሎች በመጽሐፍ ከጻፈ ከፈጸመም በኋላ፥
25 ፤ ሙሴ የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን ታቦት የሚሸከሙትን ሌዋውያንን እንዲህ ብሎ አዘዘ።
26 ፤ ይህን የሕግ መጽሐፍ ውሰዱ፥ በዚያም በእናንተ ላይ ምስክር እንዲሆን በአምላካችሁ በእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ታቦት አጠገብ አኑሩት።
27 ፤ እኔ ዓመፃችሁንና የአንገታችሁን ድንዳኔ አውቃለሁና፤ እኔም ዛሬ ከእናንተ ጋር ገና በሕይወት ሳለሁ እናንተ በእግዚአብሔር ላይ ዐምፃችኋል፤ ይልቁንስ ከሞትሁ በኋላ እንዴት ይሆናል?
28 ፤ ይህን ቃል በጆሮአቸው እናገር ዘንድ፥ ሰማይንና ምድርንም አስመሰክርባቸው ዘንድ የነገዶቻችሁን ሽማግሌዎች ሁሉ አለቆቻችሁንም ሰብስቡልኝ፤
29 ፤ ከሞትሁ በኋላ ፈጽማችሁ እንድትረክሱ፥ ካዘዝኋችሁም መንገድ ፈቀቅ እንድትሉ አውቃለሁና። በእጃችሁም ሥራ ታስቈጡት ዘንድ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ስላደረጋችሁ በኋለኛው ዘመን ክፉ ነገር ያገኛችኋል።
30 ፤ ሙሴም በእስራኤል ጉባኤ ሁሉ ጆሮ የዚህች መዝሙር ቃሎች እስኪፈጸሙ ድረስ ተናገረ።