ምዕራፍ 26

አምላክህ እግዚአብሔር ርስት አድርጎ ወደሚሰጥህ ምድር በገባህም ጊዜ፥ በወረስሃትም በኖርህባትም ጊዜ፥
2 ፤ አምላክህ እግዚአብሔር ከሚሰጥህ ምድር ከምትሰበስበው ፍሬ ሁሉ በኵራት ውሰድ በዕንቅብም አድርገው፥ አምላክህ እግዚአብሔር ስሙ ይጠራበት ዘንድ ወደ መረጠውም ስፍራ ይዘህ ሂድ።
3 ፤ በዚያም ወራት ወደሚሆነው ካህን መጥተህ። እግዚአብሔር ይሰጠን ዘንድ ለአባቶቻችን ወደ ማለላቸው ምድር እንደ ገባሁ ዛሬ በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት አስታውቃለሁ በለው።
4 ፤ ካህኑም ዕንቅቡን ከእጅህ ወስዶ በአምላክህ በእግዚአብሔር መሠውያ ፊት ያኑረው።
5 ፤ በአምላክህም በእግዚአብሔር ፊት እንዲህ ብለህ ተናገር። አባቴ የተቅበዘበዘ ሶርያዊ ነበረ፤ በቍጥር ጥቂት ሳለ ወደ ግብፅ ወረደ በዚያም ተቀመጠ፤ ታላቅ የሆነ የበረታም ቍጥሩም የበዛ ሕዝብ ሆነ።
6 ፤ ግብፃውያንም ክፉ ነገር አደረጉብን፥ አስጨነቁንም፥ በላያችንም ጽኑ ከባድ ሥራን ጫኑብን፤
7 ፤ ወደ አባቶቻችንም አምላክ ወደ እግዚአብሔር ጮኽን፤ እግዚአብሔርም ድምፃችንን ሰማ፥ ጭንቀታችንንም ድካማችንንም ግፋችንንም አየ፤
8 ፤ እግዚአብሔርም በጸናች እጅና በተዘረጋ ክንድ፥ በታላቅም ድንጋጤ፥ በተአምራትም፥ በድንቅም ከግብፅ አወጣን፤
9 ፤ ወደዚህም ስፍራ አገባን፥ ወተትና ማር የምታፈስሰውንም ይህችን ምድር ሰጠን።
10 ፤ አሁንም እነሆ፥ አቤቱ፥ አንተ የሰጠኸኝን የምድሪቱን ፍሬ በኵራት አቅርቤአለሁ። አንተም በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት አኑረው፥ በአምላክህም በእግዚአብሔር ፊት ስገድ።
11 ፤ አንተም በመካከልህም ያለ ሌዋዊና መጻተኛ አምላክህ እግዚአብሔር ለአንተና ለቤትህ በሰጠው ቸርነት ሁሉ ደስ ይበላችሁ።
12 ፤ አሥራት በምታወጣበት በሦስተኛው ዓመት የፍሬህን ሁሉ አሥራት አውጥተህ በፈጸምህ ጊዜ፥ በአገርህ ደጅ ውስጥ ይበሉ ዘንድ ይጠግቡም ዘንድ ለሌዋዊው ለመጻተኛውም ለድሀ አደጉም ለመበለቲቱም ስጣቸው።
13 ፤ በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት እንዲህ በል። የተቀደሰውን ነገር ከቤቴ ወስጄ ለሌዋዊው ለመጻተኛውም ለድሀ አደጉም ለመበለቲቱም እንዳዘዝኸኝ ትእዛዝ ሁሉ ሰጥቼአለሁ፤ ትእዛዝህን ምንም አላፈረስሁም፥ አልረሳሁምም፤
14 ፤ በኀዘኔ ጊዜ እኔ ከእርሱ አልበላሁም፥ ለርኵስነቴም ከእርሱ አላወጣሁም፥ ከእርሱም አንዳች ለሞተ ሰው አልሰጠሁም፤ የአምላኬንም የእግዚአሔርን ቃል ሰምቼአለሁ፥ ያዘዝኸኝንም ሁሉ አድርጌአለሁ።
15 ፤ ከቅዱስ ማደሪያህ ከሰማይ ጐብኝ፥ ሕዝብህንም እስራኤልን ለአባቶቻችን እንደ ማልህላቸው የሰጠኸንንም ወተትና ማር የምታፈስሰውን አገር ባርክ።
16 ፤ አምላክህ እግዚአብሔር ይህን ሥርዓትና ፍርድ ታደርግ ዘንድ ዛሬ አዝዞሃል፤ አንተም በፍጹም ልብህና በፍጹም ነፍስህ ጠብቀው፥ አድርገውም።
17 ፤ አንተ በመንገዱ ትሄድ ዘንድ፥ ሥርዓቱንና ትእዛዙን ፍርዱንም ትጠብቅ ዘንድ፥ ቃሉንም ትሰማ ዘንድ እግዚአብሔር እርሱ አምላክህ መሆኑን ዛሬ አስታውቀሃል።
18 ፤ እግዚአብሔርም እንደ ሰጠህ ተስፋ ገንዘቡና ሕዝቡ መሆንህን፥ ትእዛዙንም ሁሉ ትጠብቅ ዘንድ፥
19 ፤ ከፈጠራቸውም አሕዛብ ሁሉ በምስጋና በስም በክብር ከፍ ያደርግህ ዘንድ፥ እርሱም እንደ ተናገረ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ሕዝብ ትሆን ዘንድ ዛሬ አስታውቆአል።