ኦሪት ዘዳግም
ምዕራፍ 32
ሰማያት ሆይ፥ አድምጡ፥ እኔም እናገራለሁ፤  ምድርም የአፌን ቃሎች ትስማ።
2 ፤ ትምህርቴ እንደ ዝናብ ትፈስሳለች፥  ነገሬ እንደ ጠል ትንጠባጠባለች፤  በልምላሜ ላይ እንደ ጤዛ፥  በሣርም ላይ እንደ ካፊያ።
3 ፤ የእግዚአብሔርን ስም እጠራለሁና፤  ለአምላካችን ታላቅነትን ስጡ።
4 ፤ እርሱ አምላክ ነው፤ ሥራውም ፍጹም ነው፤  መንገዱም ሁሉ የቀና ነው፤  የታመነ አምላክ፥ ክፋትም የሌለበት፥  እርሱ እውነተኛና ቅን ነው።
5 ፤ እነርሱ ረከሱ፤ ልጆቹም አይደሉም፤  ነውርም አለባቸው፤ ጠማማና ገልበጥባጣ ትውልድ ናቸው።
6 ፤ ደንቆሮ ብልሃተኛም ያልሆንህ ሕዝብ ሆይ፥  ለእግዚአብሔር ይህንን ትመልሳለህ?  የገዛህ አባትህ አይደለምን?  የፈጠረህና ያጸናህ እርሱ ነው።
7 ፤ የዱሮውን ዘመን አስብ፥  የብዙ ትውልድንም ዓመታት አስተውል፤  አባትህን ጠይቅ፥ ያስታውቅህማል፤  ሽማግሌዎችህን ጠይቅ፥ ይነግሩህማል።
8 ፤ ልዑል ለአሕዛብ ርስታቸውን ባወረሰ ጊዜ፥  የአዳምን ልጆች በለየ ጊዜ፥  እንደ እስራኤል ልጆች ቍጥር  የአሕዛብን ድንበር አቆመ።
9 ፤ የእግዚአብሔር እድል ፈንታ ሕዝቡ ነው፤  ያዕቆብም የርስቱ ገምድ ነው።  
10 ፤ በምድረ በዳ በጥማት፥  የነፋስ ጩኸትም በሞላበት ውድማ አገኘው፤  ከበበው ተጠነቀቀለትም፤  እንደ ዓይን ብሌን ጠበቀው።  
11 ፤ ንስር ጫጩቶቹን እንደሚያወጣ፥  በእነርሱም ላይ እንደሚሰፍፍ፥  ክንፎቹን ዘርግቶ ወሰዳቸው፥  በክንፎቹም አዘላቸው።  
12 ፤ እግዚአብሔር ብቻውን መራው፤  ከእርሱም ጋር ሌላ አምላክ አልነበረም።  
13 ፤ በምድር ከፍታ ላይ አወጣው፤  የእርሻውን ፍሬ በላ፤  ከዓለትም ድንጋይ በሚገኝ ማር፥  ከጭንጫውም ድንጋይ በሚገኝ ዘይት አጠባው፤  
14 ፤ የላሙንም ቅቤ፥ የመንጋውም ወተት፥  ከጠቦት ስብ ጋር፥  የባሳንንም አውራ በግ፥ ፍየሉንም፥  ከስንዴ እሸት ጋር በላህ፤  ከወይኑም ደም ያለውን ጠጅ ጠጣህ።  
15 ፤ ይሹሩን ወፈረ፥ ረገጠ፤  ወፈረ፥ ደነደነ፥ ሰባ፤  የፈጠረውንም እግዚአብሔርን ተወ፤  የመድኃኒቱንም አምላክ ናቀ።  
16 ፤ በሌሎች አማልክት አስቀኑት፥  በርኵሰታቸውም አስቈጡት።  
17 ፤ እግዚአብሔር ላልሆኑ አጋንንት፥  ለማያውቋቸውም አማልክት፥  በቅርብ ጊዜ ለተነሡ ለአዲሶች  አባቶቻቸውም ላልፈሩአቸው አማልክት ሠዉ።  
18 ፤ የወለደህን አምላክ ተውህ፥  ያሳደገህን እግዚአብሔርን ረሳህ።  
19 ፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆችም ስላስቈጡት  እግዚአብሔር አይቶ ጣላቸው።  
20 ፤ እርሱም አለ። ፊቴን እሰውርባቸዋለሁ፤  ፍጻሜያቸው ምን እንደ ሆነ አያለሁ፤  ጠማማ ትውልድ፥  ያልታመኑም ልጆች ናቸው።  
21 ፤ አምላክ ባልሆነው አስቀኑኝ፤ 3 ቍ.15፤ በዕብራይስጥ ይሹሩን የሚለውን ግዕዙ ያዕቆብ ይለዋል።  በምናምንቴዎቻቸውም አስቈጡኝ፤  እኔም ሕዝብ ባልሆነው አስቀናቸዋለሁ፤  በማያስተውል ሕዝብ አስቈጣቸዋለሁ።  
22 ፤ እሳት ከቍጣዬ ትነድዳለችና፥  እስከ ሲኦል ድረስ ታቃጥላለች፥  ምድርንም ከፍሬዋ ጋር ትበላለች፥  የተራሮችን መሠረት ታነድዳለች።  
23 ፤ መከራን እጨምርባቸዋለሁ፤  በፍላጾቼም እወጋቸዋለሁ።  
24 ፤ በራብ በንዳድ ይጠፋሉ፤  በንዳድና በመራራ ጥፋት ያልቃሉ፤  የአራዊትን ጥርስ፥  የምድርንም እባብ መርዝ እሰድድባቸዋለሁ።  
25 ፤ ጕልማሳውን ከድንግል፥ ሕፃኑንም ከሽማግሌ ጋር፥  በሜዳ ሰይፍ፥ በቤትም ውስጥ ድንጋጤ ያጠፋቸዋል።  
26 ፤ እበትናቸዋለሁ አልሁ፤  ከሰዎችም መካከል መታሰቢያቸውን አጠፋለሁ።  
27 ፤ ነገር ግን ጠላቶቻቸው እንዳይታበዩ።  እጃችን ከፍ ከፍ አለች እንጂ  እግዚአብሔር ይህን ሁሉ አላደረገም  እንዳይሉ፥  ስለ ጠላቱ ቍጣ ፈራሁ።  
28 ፤ ምክር ያጡ ሕዝብ ናቸው፥  ማስተዋልም የላቸውም።  
29 ፤ አእምሮ ቢኖራቸው፥  ይህንን ያስተውሉ ነበር፥  ፍጻሜያቸውንም ያስቡ ነበር።  
30 ፤ እርሱ አምላካቸው ካልሸጣቸው፥  እግዚአብሔርም አሳልፎ ካልሰጣቸው፥  አንድ ሰው እንዴት ሺህን ያሳድድ ነበር?  ሁለቱሳ እንዴት አሥሩን ሺህ ያሸሹ ነበር?  
31 ፤ አምላካችን እንደ አማልክቶቻቸው አይደለም፤  ጠላቶቻችንም ሰነፎች ናቸው።  
32 ፤ ወይናቸው ከሰዶም ወይን፥  ከገሞራም እርሻ ነው፤  ፍሬያቸው ሐሞት ነው፤  ዘለላውም መራራ ነው።  
33 ፤ የወይን ጠጃቸው የእባብ መርዝ፥  የእፉኝትም ሥራይ ነው።  
34 ፤ ይህ በእኔ ዘንድ ተጠብቆ የለምን?  በመዝገቤስ የታተመ አይደለምን?  
35 ፤ የጥፋታቸው ቀን ቀርቦአልና፥  የሚመጣባቸውም ነገር ይፈጥናልና  እግራቸው ሲሰናከል  በቀልና ፍርድ የእኔ ነው።  
36 ፤ ኃይላቸውም እንደ ደከመ፥  የተዘጋ የተለቀቀም እንደሌለ ባየ ጊዜ  እግዚአብሔር ለሕዝቡ ይፈርዳል፥  ስለ ባሪያዎቹም ያዝናል።  
37 ፤ እርሱም ይላል። አማልክቶቻቸው የት ናቸው?  ይታመኑባቸው የነበሩት አማልክት?  
38 ፤ የመሥዋዕታቸውን ስብ የበሉ፥  የመጠጥ ቍርባናቸውንም የወይን ጠጅ የጠጡ?  እነርሱ ይነሡ፥ ይርዱአችሁም፥  መጠጊያም ይሁኑላችሁ።  
39 ፤ አሁንም እኔ ብቻዬን እኔ እንደ ሆንሁ፥  ከእኔም በቀር አምላክ እንደሌለ እዩ፤  እኔ እገድላለሁ፥ አድንማለሁ፤  እኔ እመታለሁ፥ እፈውስማለሁ፤  ከእጄም የሚያድን የለም።  
40 ፤ እጄን ወደ ሰማይ እዘረጋለሁና፥  እንዲህም እላለሁ። ለዘላለም እኔ ሕያው ነኝና  
41 ፤ የሚንቦገቦግ ሰይፌን እስለዋለሁ፥  እጄም ፍርድን ትይዛለች፥  ጠላቶቼንም እበቀላለሁ፥  ለሚጠሉኝም ፍዳቸውን እከፍላለሁ።  
42 ፤ ከተወጉት ከተማረኩትም ደም፥  ፍላጾቼን በደም አሰክራለሁ፤  ከጠላት አለቆችም ራስ  ሰይፌ ሥጋ ይበላል።  
43 ፤ የባሪያዎቹን ደም ይበቀላልና፥  ጠላቶቹንም ይበቀላቸዋልና፥  ምድሪቱንና ሕዝቡን ይክሳልና  እናንተ አሕዛብ ሆይ፥ ከሕዝቡ ጋር ደስ ይበላችሁ።
44 ፤ ሙሴም የነዌም ልጅ ኢያሱ የዚህችን መዝሙር ቃሎች ሁሉ በሕዝቡ ጆሮ ተናገሩ።
45 ፤ ሙሴም ይህን ቃል ሁሉ ለእስራኤል ሁሉ ተናግሮ ፈጸመ።
46 ፤ እርሱም እንዲህ አላቸው። የዚህን ሕግ ቃሎች ሁሉ ይጠብቁና ያደርጉ ዘንድ ልጆቻችሁን እንድታዝዙበት ዛሬ የምመሰክርላችሁን ቃል ሁሉ በልባችሁ አኑሩት።
47 ፤ ይህ ነገር ሕይወታችሁ ነው እንጂ ለእናንተ ከንቱ አይደለምና፤ በዚህም ነገር ትወርሱአት ዘንድ ዮርዳኖስን ተሻግራችሁ በምትገቡባት ምድር ረጅም ዘመን ትቀመጣላችሁ።
48 ፤ በዚያም ቀን እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።
49 ፤ ወደዚህ በኢያሪኮ አንጻር በሞዓብ ምድር በዓባሪም ተራራ ውስጥ ወዳለው ወደ ናባው ተራራ ውጣ፥ ለእስራኤልም ልጆች ርስት አድርጌ የምሰጣቸውን የከነዓንን ምድር እይ፤
50 ፤ ወንድምህም አሮን በሖር ተራራ እንደ ሞተ ወደ ወገኖቹም እንደ ተከማቸ፥ በወጣህበት ተራራ ሙት፥ ወደ ወገኖችህም ተከማች፤
51 ፤ በእስራኤል ልጆች መካከል በጺን ምድረ በዳ በቃዴስ ባለው በመሪባ ውኃ ስለ በደላችሁኝ፥ በእስራኤልም ልጆች መካከል ስላልቀደሳችሁኝ፥
52 ፤ ምድሪቱን ፊት ለፊት ታያለህ እንጂ ወደዚያች እኔ ለእስራኤል ልጆች ወደምሰጣቸው ምድር አትገባም።