ምዕራፍ 27

ሙሴና የእስራኤል ሽማግሌዎችም እንዲህ ብለው ሕዝቡን አዘዙ። ዛሬ ያዘዝኋችሁን ትእዛዝ ሁሉ ጠብቁ።
2 ፤ አምላክህ እግዚአብሔር ወደሚሰጥህ ምድር ዮርዳኖስን በተሻገርህ ጊዜ ታላላቅ ድንጋዮችን ለአንተ አቁም፥ በኖራም ምረጋቸው።
3 ፤ የአባቶችህ አምላክ እግዚአብሔር ተስፋ እንደ ሰጠህ፥ ወተትና ማር ወደምታፈስስ ምድር፥ አምላክህ እግዚአብሔር ወደሚሰጥህ ምድር ትገባ ዘንድ በተሻገርህ ጊዜ፥ የዚህን ሕግ ቃሎች ሁሉ ጻፍባቸው።
4 ፤ ዮርዳኖስንም በተሻገርህ ጊዜ፥ ዛሬ እንዳዘዝሁህ፥ እነዚህን ድንጋዮች በጌባል ተራራ አቁም፥ በኖራም ምረጋቸው።
5 ፤ በዚያም ለአምላክህ ለእግዚአብሔር መሠዊያ ሥራ፤ መሠዊያውም ብረት ካልነካው ድንጋይ ይሁን።
6 ፤ ካልተጠረበም ድንጋይ የአምላክህን የእግዚአብሔርን መሠዊያ ሥራ፤ ለአምላክም ለእግዚአብሔር የሚቃጠለውን መሥዋዕትህን አቅርብበት፤
7 ፤ የደኅንነትም መሥዋዕት ሠዋበት፥ በዚያም ብላ፤ በአምላክህም በእግዚአብሔር ፊት ደስ ይበልህ።
8 ፤ የዚህንም ሕግ ቃሎች ሁሉ የተገለጠ አድርገህ በድንጋዮቹ ላይ ጻፍ።
9 ፤ ሙሴና ሌዋውያን ካህናት ለእስራኤል ሁሉ እንዲህ ብለው ተናገሩ። እስራኤል ሆይ፥ ዝም ብላችሁ አድምጡ፤ ዛሬ የአምላክህ የእግዚአብሔር ሕዝብ ሆነሃል።
10 ፤ ለአምላክህም ለእግዚአብሔር ቃል ታዘዝ፥ ዛሬም የማዝዝህን ትእዛዙንና ሥርዓቱን አድርግ።
11 ፤ ሙሴም በዚያን ቀን እንዲህ ብሎ ሕዝቡን አዘዘ።
12 ፤ ዮርዳኖስን በተሻገራችሁ ጊዜ ሕዝቡን ይባርኩ ዘንድ እነዚህ፥ ስምዖንና ሌዊ ይሁዳና ይሳኮር ዮሴፍና ብንያም፥ በገሪዛን ተራራ ላይ ይቁሙ።
13 ፤ ይረግሙም ዘንድ እነዚህ፥ ሮቤልና ጋድ አሴርና ዛብሎን ዳንና ንፍታሌም፥ በጌባል ተራራ ላይ ይቁሙ።
14 ፤ ሌዋውያንም ከፍ ባለች ድምፅ ለእስራኤል ሰዎች ሁሉ እንዲህ ብለው ይናገራሉ።
15 ፤ በእግዚአብሔር ዘንድ የተጠላ የሠራተኛ እጅ ሥራን የተቀረጸ ወይም ቀልጦ የተሠራ ምስልን የሚያደርግ፥ በስውርም የሚያቆመው ሰው ርጉም ይሁን፤ ሕዝቡም ሁሉ መልሰው አሜን ይላሉ።
16 ፤ አባቱን ወይም እናቱን የሚያቃልል ርጉም ይሁን፤ ሕዝቡም ሁሉ አሜን ይላሉ።
17 ፤ የባልንጀራውን የድንበር ምልክት የሚገፋ ርጉም ይሁን፤ ሕዝቡም ሁሉ አሜን ይላሉ።
18 ፤ ዕውሩን ከመንገድ ፈቀቅ የሚያደርግ ርጉም ይሁን፤ ሕዝቡም ሁሉ አሜን ይላሉ።
19 ፤ በመጻተኛ በድሀ አደጉም በመበለቲቱም ላይ ፍርድን የሚያጣምም ርጉም ይሁን፤ ሕዝቡም ሁሉ አሜን ይላሉ።
20 ፤ ከአባቱ ሚስት ጋር የሚተኛ የአባቱን ልብስ ገልጦአልና ርጉም ይሁን፤ ሕዝቡም ሁሉ አሜን ይላሉ።
21 ፤ ከማናቸይቱም እንስሳ ጋር የሚተኛ ርጉም ይሁን፤ ሕዝቡም ሁሉ አሜን ይላሉ።
22 ፤ ከአባቱ ወይም ከእናቱ ልጅ ከእኅቱ ጋር የሚተኛ ርጉም ይሁን፤ ሕዝቡም ሁሉ አሜን ይላሉ።
23 ፤ ከአማቱ ጋር የሚተኛ ርጉም ይሁን፤ ሕዝቡም ሁሉ አሜን ይላሉ።
24 ፤ ባልንጀራውን በስውር የሚመታ ርጉም ይሁን፤ ሕዝቡም ሁሉ አሜን ይላሉ።
25 ፤ የንጹሑን ሰው ነፍስ ለመግደል ጉቦ የሚቀበል ርጉም ይሁን፤ ሕዝቡም ሁሉ አሜን ይላሉ።
26 ፤ የዚህን ሕግ ቃሎች ያደርግ ዘንድ የማያጸና ርጉም ይሁን፤ ሕዝቡም ሁሉ አሜን ይላሉ።