ትንቢተ ሚክያስ

1 2 3 4 5 6 7


ምዕራፍ 6

አሁን። ተነሣ፥ በተራሮችም ፊት ተፋረድ፥ ኮረብቶችም ቃልህን ይስሙ ብሎ እግዚአብሔር የሚለውን ስሙ።
2 ፤ ተራሮች ሆይ፥ ጠንካሮች የምድር መሠረቶችም ሆይ፥ እግዚአብሔር ከሕዝቡ ጋር ክርክር አለውና፥ ከእስራኤልም ጋር ይፋረዳልና የእግዚአብሔርን ክርክር ስሙ።
3 ፤ ሕዝቤ ሆይ፥ ምን አድርጌሃለሁ? በምንስ አድክሜሃለሁ? መስክርብኝ።
4 ፤ ከግብጽ ምድር አውጥቼሃለሁ፥ ከባርነት ቤትም ተቤዥቼሃለሁ፤ በፊትህም ሙሴንና አሮንን ማርያምንም ልኬልህ ነበር።
5 ፤ ሕዝቤ ሆይ፥ የሞዓብ ንጉሥ ባላቅ የመከረውን፥ የቢዖርም ልጅ በለዓም የመለሰለትን አሁን አስብ፤ የእግዚአብሔርንም የጽድቅ ሥራ ታውቅ ዘንድ ከሰጢም ጀምሮ እስከ ጌልገላ ድረስ አስብ።
6 ፤ ምን ይዤ ወደ እግዚአብሔር ፊት ልምጣና በልዑል አምላክ ፊት ልስገድ? የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የአንዱን ዓመት ጥጃ ይዤ በፊቱ ልምጣን?
7 ፤ እግዚአብሔርስ በሺህ አውራ በጎች ወይስ በእልፍ የዘይት ፈሳሾች ደስ ይለዋልን? ወይስ የበኵር ልጄን ስለ በደሌ፥ የሆዴንም ፍሬ ስለ ነፍሴ ኃጢአት እሰጣለሁን?
8 ፤ ሰው ሆይ፥ መልካሙን ነግሮሃል፤ እግዚአብሔርም ከአንተ ዘንድ የሚሻው ምንድር ነው? ፍርድን ታደርግ ዘንድ፥ ምሕረትንም ትወድድ ዘንድ፥ ከአምላክህም ጋር በትሕትና ትሄድ ዘንድ አይደለምን?
9 ፤ የእግዚአብሔር ድምፅ ከተማይቱን ይጠራታል፤ ስምህን መፍራት ጥበብ ነው፤ የመቅሠፍትን በትር፥ እርሱንም ያዘጋጀ ማን እንደ ሆነ ስሙ።
10 ፤ በውኑ በኃጢአተኛ ቤት የኃጢአት መዝገብ፥ የተጸየፈም ውሽተኛ መስፈሪያ ገና አለ ይሆን?
11 ፤ በአባይ ሚዛንና በከረጢት ባለ በተንኰል መመዘኛ ንጹሕ እሆናለሁን?
12 ፤ ባለ ጠጎችዋን ግፍ ሞልቶባቸዋል፤ በእርስዋም የሚኖሩ በሐሰት ተናግረዋል፥ ምላሳቸውም በአፋቸው ውስጥ ተንኰለኛ ነው።
13 ፤ ስለዚህ እኔ ደግሞ በክፉ ቍስል መታሁህ፤ ስለ ኃጢአትህም አፈርስሁህ።
14 ፤ ትበላለህ፥ ነገር ግን አትጠግብም፥ ችጋርህም በመካከልህ ይሆናል፤ ትወስዳለህ፥ ነገር ግን አታድንም፤ የምታድነውንም ለሰይፍ እሰጣለሁ።
15 ፤ ትዘራለህ፥ ነገር ግን አታጭድም፤ ወይራውንም ትጨምቃለህ፥ ነገር ግን ዘይቱን አትቀባም፤ ወይኑንም ትጨምቃለህ፥ ነገር ግን የወይን ጠጁን አትጠጣም።
16 ፤ አንተን ለጥፋት፥ በእርስዋም የሚኖሩትን ለማፍዋጫ እሰጥ ዘንድ የዘንበሪን ሥርዓትና የአክዓብን ቤት ሥራ ሁሉ ጠብቃችኋል፥ በምክራቸውም ሄዳችኋል፤ የሕዝቤንም ስድብ ትሸከማላችሁ።