ትንቢተ ሚክያስ
ምዕራፍ 1
በይሁዳ ነገሥታት በኢዮአታምና በአካዝ በሕዝቅያስም ዘመን ወደ ሞሬታዊው ወደ ሚክያስ የመጣው፥ ስለ ሰማርያና ስለ ኢየሩሳሌም ያየው፥ የእግዚአብሔር ቃል ይህ ነው።
2 ፤ እናንተ አሕዛብ ሁሉ፥ ስሙ፤ ምድርም ሙላዋም ታድምጥ፤ ጌታ እግዚአብሔርም፥ እርሱም በቅዱስ መቅደሱ የሆነ ጌታ፥ ይመስክርባችሁ።
3 ፤ እነሆ፥ እግዚአብሔር ከስፍራው ይወጣል፥ ወርዶም በምድር ከፍታዎች ላይ ይረግጣል።
4 ፤ ተራሮችም በእሳት ፊት እንዳለ ሰም፥ በገደልም ወርዶ እንደሚፈስስ ውኃ፥ በበታቹ ይቀልጣሉ፥ ሸለቆችም ይሰነጠቃሉ።
5 ፤ ይህ ሁሉ ስለ ያዕቆብ በደልና ስለ እስራኤል ቤት ኃጢአት ነው። የያዕቆብም በደል ምንድር ነው? ሰማርያ አይደለችምን? የይሁዳስ የኮረብታው መስገጃ ምንድር ነው? ኢየሩሳሌም አይደለችምን?
6 ፤ ስለዚህ ሰማርያን በሜዳ እንደሚገኝ የድንጋይ ክምር፥ ወይን እንደሚተከልበትም ስፍራ አደርጋታለሁ፤ ድንጋዮችዋንም ወደ ሸለቆ እወረውራለሁ፥ መሠረቶችዋንም እገልጣለሁ።
7 ፤ የተቀረጹትም ምስሎችዋ ይደቅቃሉ፥ በግልሙትና ያገኘችው ዋጋ ሁሉ በእሳት ይቃጠላል፥ ጣዖታትዋንም ሁሉ አጠፋለሁ፤ በግልሙትና ዋጋ ሰበሰበቻቸው፥ ወደ ግልሙትናም ዋጋ ይመለሳሉና።
8 ፤ ስለዚህ ነገር ዋይ ብላ ታለቅሳለች፥ ባዶ እግርዋንና ዕራቁትዋን ሆና ትሄዳለች፤ እንደ ቀበሮ ታለቅሳለች፥ እንደ ሰጐንም ዋይ ትላለች፤
9 ፤ ቍስልዋ የማይፈወስ ነውና፤ እስከ ይሁዳም ደርሶአልና፥ ወደ ሕዝቤም በር ወደ ኢየሩሳሌም ቀርቦአልና።
10 ፤ በጌት ላይ አታውሩ፤ በአኮ ላይ እንባን አታድርጉ፤ በቤትዓፍራ በትቢያ ላይ ተንከባለሉ።
11 ፤ በሻፊር የምትቀመጪ ሆይ፥ በዕራቁትነትሽና በእፍረት እለፊ፤ በጸዓናን የምትቀመጠው አልወጣችም፤ የቤትኤጼል ልቅሶ ከእናንተ ዘንድ መኖሪያውን ይወስዳል።
12 ፤ ክፉ ነገር ከእግዚአብሔር ዘንድ እስከ ኢየሩሳሌም በር ድረስ ወርዶአልና በማሮት የምትቀመጠው በጎነትን ትጠባበቃለች።
13 ፤ በለኪሶ የምትቀመጪ ሆይ፥ ሰረገላውን ለፈረስ እሰሪ፤ እርስዋ ለጽዮን ሴት ልጅ የኃጢአት መጀመሪያ ነበረች፤ የእስራኤል በደል በአንቺ ዘንድ ተገኝቶአልና።
14 ፤ ስለዚህ ትሎት ለሞሬሼትጌት ትሰጪአለሽ፤ የአክዚብ ቤቶች ለእስራኤል ነገሥታት አታላይ ይሆናሉ።
15 ፤ በመሪሳ የምትቀመጪ ሆይ፥ ወራሽ አመጣብሻለሁ፤ የእስራኤል ክብር ወደ ዓዶላም ይመጣል።
16 ፤ ተማርከው ከአንቺ ዘንድ ወጥተዋልና ስለ ተድላሽ ልጆች ራስሽን ንጪ፥ ጠጕርሽንም ተቈረጪ፤ ቡሃነትሽንም እንደ ንስር አስፊ።