ትንቢተ ሚክያስ

1 2 3 4 5 6 7


ምዕራፍ 3

እንዲህም አልሁ። የያዕቆብ አለቆችና የእስራኤል ቤት ገዦች ሆይ፥ እባካችሁ ስሙኝ፤ ፍርድን ታውቁ ዘንድ አይገባችሁምን?
2 ፤ መልካሙን ጠልታችኋል፥ ክፉውንም ወድዳችኋል፤ ቁርበታቸውን ገፍፋችኋቸዋል፥ ሥጋቸውንም ከአጥንታቸው ለያይታችኋል፤
3 ፤ የሕዝቤን ሥጋ በልታችኋል፥ ቁርበታቸውንም ገፍፋችኋቸዋል፥ አጥንታቸውንም ሰብራችኋል፤ ለአፍላል እንደሚሆን ሥጋ ለድስትም እንደሚሆን ሙዳ ቈራረጣችኋቸው።
4 ፤ የዚያን ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ይጮኻሉ፥ እርሱም አይሰማቸውም፤ ሥራቸውንም ክፉ አድርገዋልና በዚያን ጊዜ ፊቱን ከእነርሱ ይሰውራል።
5 ፤ እግዚአብሔር ሕዝቤን ስለሚያስቱ ነቢያት እንዲህ ይላል፤ በጥርሳቸው ሲነክሱ በሰላም ይሰብካሉ፤ በአፋቸው ግን አንዳች በማይሰጥ ሰው ላይ ሰልፍን ያስቡበታል።
6 ፤ ስለዚህ ሌሊት ይሆንባችኋል እንጂ ራእይ አይሆንላችሁም፤ ጨለማም ይሆንባችኋል እንጂ አታምዋርቱም፤ ፀሐይም በነቢያት ላይ ትገባለች፥ ቀኑም ይጠቁርባቸዋል።
7 ፤ ከእግዚአብሔርም ዘንድ መልስ የለምና ባለ ራእዩቹ ያፍራሉ፥ ምዋርተኞችም ይዋረዳሉ፤ ሁሉም ከንፈራቸውን ይሸፍናሉ።
8 ፤ እኔ ግን በደሉን ለያዕቆብ፥ ኃጢአቱንም ለእስራኤል እነግር ዘንድ በእግዚአብሔር መንፈስ ኃይልንና ፍርድን ብርታትንም ተሞልቻለሁ።
9 ፤ ፍርድን የምትጠሉ ቅን ነገርንም ሁሉ የምታጣምሙ እናንተ የያዕቆብ ቤት አለቆችና የእስራኤል ቤት ገዦች ሆይ፥ እባካችሁ ይህን ስሙ።
10 ፤ ጽዮንን በደም፥ ኢየሩሳሌምንም በኃጢአት ይሠራሉ።
11 ፤ አለቆችዋ በጉቦ ይፈርዳሉ፥ ካህናቶችዋም በዋጋ ያስተምራሉ፥ ነቢያቶችዋም በገንዘብ ያምዋርታሉ፤ ከዚህም ጋር። እግዚአብሔር በመካከላችን አይደለምን? ክፉ ነገር ምንም አይመጣብንም እያሉ በእግዚአብሔር ይታመናሉ።
12 ፤ ስለዚህ በእናንተ ምክንያት ጽዮን እንደ እርሻ ትታረሳለች፥ ኢየሩሳሌምም የድንጋይ ክምር ትሆናለች፥ የቤቱም ተራራ እንደ ዱር ከፍታ ይሆናል።