ትንቢተ ሚክያስ

1 2 3 4 5 6 7


ምዕራፍ 2

በመኝታቸው ላይ በደልን ለሚያስቡ ክፋትንም ለሚያደርጉ ወዮላቸው! ኃይል በእጃቸው ነውና ሲነጋ ይፈጽሙታል።
2 ፤ በእርሻው ላይ ይመኛሉ፥ በግዴታም ይይዙታል፤ በቤቶችም ላይ ይመኛሉ፥ ይወስዱአቸውማል፤ ሰውንና ቤቱን፥ ሰውንና ርስቱንም ይነጥቃሉ።
3 ፤ ስለዚህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ በዚህ ወገን ላይ በክፉ አስባለሁ፥ ከዚያም አንገታችሁን አታነሡም፤ ዘመኑም ክፉ ነውና ቀጥ ብላችሁ አትሄዱም።
4 ፤ በዚያ ቀን በምሳሌ ይመስሉባችኋል፥ በጽኑ ልቅሶም ያለቅሱላችኋል፤ እነርሱም። ፈጽመን ጠፍተናል፤ የሕዝቤን እድል ፈንታ ይሰፍራል፥ እርሱንም የሚከለክል የለም፤ እርሻችንን ለዓመፀኞች ይከፍላል ይላሉ።
5 ፤ ስለዚህ በእግዚአብሔር ጉባኤ መካከል በዕጣ ገመድ የሚጥል አይኖርህም።
6 ፤ ትንቢት አትናገሩ ብለው ይናገራሉ፤ በእነዚህ ላይ ትንቢት አይናገሩም፥ ስድብም አይርቅም።
7 ፤ የያዕቆብ ቤት የተባልህ ሆይ፥ በውኑ የእግዚአብሔር መንፈስ የማይታገሥ ነውን? ወይስ ሥራው እንደዚች ናትን? ቃሌስ በቅን ለሚሄድ በጎነት አያደርግምን?
8 ፤ ነገር ግን ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ ሕዝቤ እንደ ጠላት ሆኖ ተነሥቶአል፤ ቀሚስንና መጐናጸፊያን ገፈፋችሁ፤ ሳይፈሩም፤ የሚያልፉትን ከሰልፍ እንደሚመለሱ አደረጋችኋቸው።
9 ፤ የሕዝቤንም ሴቶች ከተሸለሙ ቤቶቻቸው አሳደዳችኋቸው፤ ከሕፃናቶቻቸውም ክብሬን ለዘላለም ወሰዳችሁ።
10 ፤ በዚህ ዕረፍት የላችሁምና ተነሥታችሁ ሂዱ፤ በርኵሰት ምክንያት ክፉ ጥፋት ታጠፋችኋለች።
11 ፤ ነፋስንም ተከትሎ። ስለ ወይን ጠጅና ስለ ስካር ትንቢት እናገርልሃለሁ ብሎ ሐሰትን የሚናገር ሰው ቢኖር እርሱ ለዚህ ሕዝብ ነቢይ ይሆናል።
12 ፤ ያዕቆብ ሆይ፥ ሁለንተናህን ፈጽሞ እሰበስባለሁ፥ የእስራኤልንም ቅሬታ ፈጽሞ አከማቻለሁ፤ እንደ ባሶራ በጎችና እንደ መንጋ በማሰማርያቸው ውስጥ በአንድነት አኖራቸዋለሁ፤ ከሰው ብዛት የተነሣ ድምፃቸውን ያሰማሉ።
13 ፤ ሰባሪው በፊታቸው ወጥቶአል፤ እነርሱም ሰብረው ወደ በሩ አልፈዋል፥ በእርሱም በኩል ወጥተዋል፤ ንጉሣቸውም በፊታቸው አልፎአል፥ እግዚአብሔርም በራሳቸው ላይ ነው።