መጽሐፈ መክብብ
ምዕራፍ 8
እንደ ጠቢብ የሆነ ሰው ማን ነው? ነገርንስ መተርጐም የሚያውቅ ማን ነው? የሰው ጥበብ ፊቱን ታበራለች፥ የፊቱንም ድፍረት ትለውጣለች።
2 ፤ እኔ። በእግዚአብሔር መሐላ ምክንያት የንጉሥን ትእዛዝ ጠብቅ እልሃለሁ።
3 ፤ የወደደውን ሁሉ ያደርጋልና ከፊቱ ትወገድ ዘንድ አትቸኵል፥ ክፉንም በማድረግ አትጽና።
4 ፤ የንጉሥ ቃል ኃይለኛ ነውና፤ ይህንስ ለምን ታደርጋለህ? ማን ይለዋል?
5 ፤ ትእዛዝን የሚጠብቅ ክፉን ነገር አያውቅም፤ የጠቢብም ልብ ጊዜንና ፍርድን ያውቃል።
6 ፤ የሰው መከራ በእርሱ ላይ እጅግ ስለ ሆነ ለነገር ሁሉ ጊዜና ፍርድ አለውና።
7 ፤ የሚሆነውንም አያውቅም፤ እንዴትስ እንደሚሆን የሚነግረው ማን ነው?
8 ፤ መንፈስን ለማስቀረት በመንፈስ ላይ ሥልጣን ያለው ሰው የለም፤ በሞቱም ቀን ሥልጣን የለውም፤ በሰልፍም ስንብቻ የለም፥ ኃጢአትም ሠሪውን አያድነውም።
9 ፤ ይህን ሁሉ አየሁ፥ ከፀሐይም በታች ወደ ተደረገው ሥራ ሁሉ ልቤን ሰጠሁ፤ ሰው ሰውን ለመጕዳት ገዢ የሚሆንበት ጊዜ አለ።
10 ፤ እንዲሁም ኀጥኣን ተቀብረው አየሁ፥ ወደ ዕረፍትም ገቡ፤ ነገር ግን ቅን አድራጊዎች ከቅድስት ስፍራ ወጡ፥ በከተማይቱም ውስጥ ተረሱ፤ ይህም ደግሞ ከንቱ ነው።
11 ፤ በክፉ ሥራ ላይ ፈጥኖ ፍርድ አይፈረድምና ስለዚህ በሰው ልጆች ውስጥ ልባቸው ክፉን ለመሥራት ጠነከረ።
12 ፤ ኃጢአተኛ መቶ ጊዜ ክፉን ቢሠራ ዘመኑም ረጅም ቢሆን፥ እግዚአብሔርን ለሚፈሩት በፊቱም ለሚፈሩት ደኅንነት እንዲሆን አውቃለሁ፤
13 ፤ ለኀጥእ ግን ደኅንነት የለውም፥ በእግዚአብሔርም ፊት አይፈራምና ዘመኑ እንደ ጥላ አትረዝምም።
14 ፤ በምድር የሚደረግ ከንቱ ነገር አለ፤ በኀጥኣን የሚደረገው ሥራ የሚደርስባቸው ጻድቃን አሉ፥ ለጻድቃንም የሚደረገው ሥራ የሚደርስላቸው ኀጥኣን አሉ፤ ይህም ደግሞ ከንቱ ነው አልሁ።
15 ፤ ከሚበላውና ከሚጠጣው ደስም ከሚለው በቀር ለሰው ከፀሐይ በታች ሌላ መልካም ነገር የለውምና እኔ ደስታን አመሰገንሁ፤ ከፀሐይም በታች ከድካሙ እግዚአብሔር በሰጠው በሕይወቱ ዘመን ይህ ደስታው ከእርሱ ጋር ይኖራል።
16 ፤ ጥበብን አውቅ ዘንድ በምድር የሚሆነውንም ድካም አይ ዘንድ ልቤን ሰጠሁ፥ በቀንና በሌሊት እንቅልፍን በዓይኑ የማያይ አለና፤
17 ፤ ከፀሐይም በታች የተደረገውን ሥራ መርምሮ ያገኝ ዘንድ ለሰው እንዳይቻለው የእግዚአብሔርን ሥራ ሁሉ አየሁ። ሰውም ሊፈልግ እጅግ ቢደክም መርምሮ አያገኘውም፤ ደግሞ ጠቢብ ሰው። ይህን አወቅሁ ቢል እርሱ ያኘው ዘንድ አይችልም።