መጽሐፈ መክብብ

1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12


ምዕራፍ 7

ከመልካም ሽቱ መልካም ስም፥ ከመወለድ ቀንም የሞት ቀን ይሻላል።
2 ፤ ወደ ግብዣ ቤት ከመሄድ ወደ ልቅሶ ቤት መሄድ ይሻላል፤ እርሱ የሰው ሁሉ ፍጻሜ ነውና፥ ሕያውም የሆነ በልቡ ያኖረዋልና።
3 ፤ ከሳቅ ኀዘን ይሻላል፥ ከፊት ኀዘን የተነሣ ልብ ደስ ይሰኛልና።
4 ፤ የጠቢባን ልብ በልቅሶ ቤት ነው፤ የሰነፎች ልብ ግን በደስታ ቤት ነው።
5 ፤ ሰው የሰነፎችን ዜማ ከሚሰማ ይልቅ የጠቢባንን ተግሣጽ መስማት ይሻለዋል።
6 ፤ ከድስት በታች እንደሚቃጠል እሾህ ድምፅ የሰነፍ ሳቅ እንዲሁ ነው፤ ይህም ደግሞ ከንቱ ነው።
7 ፤ ግፍ ጠቢቡን ያሳብደዋል፤ ጉቦም ልቡን ያጠፋዋል።
8 ፤ የነገር ፍጻሜ ከመጀመሪያው ይሻላል፤ ታጋሽም ከትዕቢተኛ ይሻላል።
9 ፤ በነፍስህ ለቍጣ ችኩል አትሁን ቍጣ በሰነፍ ብብት ያርፋልና።
10 ፤ ከዚህ ዘመን ይልቅ ያለፈው ዘመን ለምን ተሻለ? ብለህ አትናገር፤ የዚህን ነገር በጥበብ አትጠይቅምና።
11 ፤ ጥበብ ከርስት ጋር መልካም ነው፤ ፀሐይንም ለሚያዩ ሰዎች ትርፍን ይሰጣል።
12 ፤ የጥበብ ጥላ እንደ ገንዘብ ጥላ ናትና፤ የእውቀትም ብልጫዋ ጥበብ ገንዘብ ላደረጋት ሕይወትን እንድትሰጥ ነው።
13 ፤ የእግዚአብሔርን ሥራ ተመልከት፤ እርሱ ጠማማ ያደረገውን ማን ሊያቀናው ይችላል?
14 ፤ በመልካም ቀን ደስ ይበልህ፤ በክፉም ቀን ተመልከት፤ ሰው ከእርሱ በኋላ መርምሮ ምንም እንዳያገኝ እግዚአብሔር ይህንም ያንም እንደዚያ ሠርቶአል።
15 ፤ ጻድቅ በጽድቁ ሲጠፋ ኀጥእም በክፋቱ እጅግ ዘመን ሲኖር፥ ይህን ሁሉ ከንቱ በሆነ ዘመኔ አየሁ።
16 ፤ እጅግ ጻድቅ አትሁን፥ እጅግ ጠቢብም አትሁን፥ እንዳትጠፋ።
17 ፤ እጅግ ክፉ አትሁን፥ እልከኛም አትሁን፥ ጊዜህ ሳይደርስ እንዳትሞት።
18 ፤ እግዚአብሔርን የሚፈራ ከሁሉ ይወጣልና ይህን ብትይዝ ከዚያም ደግሞ እጅህን ባታርቅ መልካም ነው።
19 ፤ በከተማ ከሚኖሩ ከአሥር ገዢዎች ይልቅ ጥበብ ጠቢብን ታበረታለች።
20 ፤ በምድር ላይ መልካምን የሚሠራ ኃጢአትንም የማያደርግ ጻድቅ አይገኝምና።
21 ፤ ባሪያህ ሲረግምህ እንዳትሰማ በሚጫወቱበት ቃል ሁሉ ልብህን አትጣል፤
22 ፤ አንተ ደግሞ ሌሎችን እንደ ረገምህ ልብህ ያውቃልና።
23 ፤ ይህን ሁሉ በጥበብ ፈተንሁ፤ ጠቢብ እሆናለሁ አልሁ፥ እርስዋ ግን ከእኔ ራቀች።
24 ፤ የሆነው ራቀ እጅግም ጠለቀ፤ መርምሮ የሚያገኘውስ ማን ነው?
25 ፤ አውቅና እመረምር ዘንድ፥ ጥበብንና የነገሩን ሁሉ መደምደሚያ እፈልግ ዘንድ፥ ኃጢአትም ስንፍና፥ ስንፍናም እብደት እንደ ሆነች አውቅ ዘንድ እኔ በልቤ ዞርሁ።
26 ፤ እኔም ከሞት ይልቅ የመረረ ነገር መርምሬ አገኘሁ፤ እርስዋም ልብዋ ወጥመድና መርበብ የሆነ፥ እጆችዋም እግር ብረት የሆኑ ሴት ናት፤ በእግዚአብሔር ፊት መልካም የሆነ ከእርስዋ ያመልጣል፥ ኃጢአተኛ ግን ይጠመድባታል።
27 ፤ አንዱን በአንዱ ላይ ጨምሬ ወደ ነገሩ ሁሉ መደምደሚያ እደርስ ዘንድ፥ እነሆ፥ ይህን ነገር አገኘሁ ይላል ሰባኪው፤
28 ፤ ነፍሴ እስከ ዛሬ ድረስ ትሻታለች፥ ነገር ግን አላገኘሁም፤ ከሺህ ወንዶች አንድ አገኘሁ፥ ከእነዚያ ሁሉ መካከል ግን አንዲት ሴት አላገኘሁም።
29 ፤ እግዚአብሔር ሰዎችን ቅኖች አድርጎ እንደ ሠራቸው፥ እነሆ፥ ይህን ብቻ አገኘሁ፤ እነርሱ ግን ብዙ ብልሃትን ፈለጉ።