መጽሐፈ መክብብ

1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12


ምዕራፍ 5

ወደ እግዚአብሔር ቤት በገባህ ጊዜ እግርህን ጠብቅ፤ ለመስማት መቅረብ ከሰነፎች መሥዋዕት ይበልጣልና፤ እነርሱም ክፉ እንዲያደርጉ አያውቁምና።
2 ፤ እግዚአብሔር በሰማይ፥ አንተም በምድር ነህና በአፍህ አትፍጠን፥ በእግዚአብሔርም ፊት ቃልን ይናገር ዘንድ ልብህ አይቸኵል፤ ስለዚህም ቃልህ ጥቂት ትሁን።
3 ፤ ሕልም በሥራ ብዛት ይታያል፤ እንዲሁም የሰነፍ ድምፅ በቃሉ ብዛት ይሰማል።
4 ፤ ሰነፎች ደስ አያሰኙትምና ለእግዚአብሔር ስእለት በተሳልህ ጊዜ ትፈጽመው ዘንድ አትዘግይ፤ የተሳልኸውን ፈጽመው።
5 ፤ ተስለህ የማትፈጽም ብትሆን ባትሳል ይሻላል።
6 ፤ ሥጋህን በኃጢአት እንዳያስተው ለአፍህ አርነት አትስጥ፥ በመልአክም ፊት። ስሕተት ነበረ አትበል፤ እግዚአብሔር በቃልህ ይቈጣ ዘንድ የእጅህንም ሥራ ያጠፋ ዘንድ ስለምን ትሻለህ?
7 ፤ ብዙ ሕልም ባለበት ዘንድ፥ እንዲሁም ደግሞ ብዙ ቃል ባለበት ስፍራ በዚያ ብዙ ከንቱ ነገር አለ፤ አንተ ግን እግዚአብሔርን ፍራ።
8 ፤ ከፍ ካለው በላይ ከፍ ያለ ይመለከታልና፥ ከእነርሱም በላይ ደግሞ ሌሎች ከፍ ይላሉና በአገሩ ድሆች ሲገፉ፥ ፍርድና ጽድቅም ሲነጠቅ ባየህ ጊዜ በዚህ ነገር አታድንቅ።
9 ፤ በጠቅላላው ግን የአገሩ ጥቅም እርሻን የሚወድድ ንጉሥ ቢኖር ነው።
10 ፤ ብርን የሚወድድ ሰው ብርን አይጠግብም፤ ባለጠግነትንም የሚወድድ ትርፉን አይጠግብም፤ ይህም ደግሞ ከንቱ ነው።
11 ፤ ሀብት ሲበዛ የሚበሉት ይበዛሉ፤ ሀብቱን በዓይኑ ብቻ ከማየት በቀር ለባለቤቱ ምን ይጠቅመዋል?
12 ፤ እጅግ ወይም ጥቂት ቢበላ የሠራተኛ እንቅልፍ ጣፋጭ ነው የባለጠጋ ጥጋብ ግን እንቅልፍን ይከለክለዋል።
13 ፤ ከፀሐይ በታች የሚያሳዝን ክፉ ነገር አየሁ፤ ለመከራው በባለቤቱ ዘንድ የተቈጠበች ባለጠግነት ናት።
14 ፤ ያችም ባለጠግነት በክፉ ነገር ትጠፋለች፤ ልጅንም ቢወልድ በእጁ ምንም የለውም።
15 ፤ ከእናቱ ሆድ ራቁቱን እንደ ወጣ እንዲሁ እንደ መጣው ይመለሳል፤ ከጥረቱም በእጁ ሊወስድ የሚችለውን ምንም አያገኝም።
16 ፤ ይህም ደግሞ የሚያሳዝን ክፉ ነገር ነው፤ እንደ መጣ እንዲሁ ይሄዳል፤ ድካሙም ለነፋስ ከሆነ ጥቅሙ ምንድር ነው?
17 ፤ ዘመኑን ሁሉ በጨለማ በኀዘን በብስጭት በደዌና በቍጣ ነው።
18 ፤ እነሆ፥ እኔ ያየሁት መልካምና የተዋበ ነገር ሰው እግዚአብሔር በሰጠው በሕይወቱ ዘመን ሁሉ ይበላና ይጠጣ ዘንድ፥ ከፀሐይ በታችም በሚደክምበት ድካም ሁሉ ደስ ይለው ዘንድ ነው፤ ይህ እድል ፈንታው ነውና።
19 ፤ እግዚአብሔር ለሰው ሁሉ ባለጠግነትንና ሀብትን መስጠቱ፥ ከእርስዋም ይበላና እድል ፈንታውን ይወስድ ዘንድ በድካሙም ደስ ይለው ዘንድ ማሠልጠኑ፤ ይህ የእግዚአብሔር ስጦታ ነው።
20 ፤ እግዚአብሔር በልቡ ደስታን ስለ ሰጠው እርሱ የሕይወቱን ዘመን እጅግ አያስብም።