መጽሐፈ መክብብ

1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12


ምዕራፍ 6

ከፀሐይ በታች ያየሁት ክፉ ነገር አለ፥ እርሱም በሰው ላይ እጅግ የከበደ ነው።
2 ፤ እግዚአብሔር ለሰው ሀብትንና ጥሪትን ክብርንም ሰጠው፥ ከወደደውም ሁሉ ለነፍሱ አልጐደለውም፤ ነገር ግን ሌላ ሰው ይበላዋል እንጂ ከእርሱ ይበላ ዘንድ እግዚአብሔር አላሠለጠነውም፤ ይህም ከንቱና ክፉ ደዌ ነው።
3 ፤ ሰው መቶ ልጆች ቢወልድ እጅግ ዘመንም በሕይወት ቢኖር ዕድሜውም እጅግ ዓመት ቢሆን፥ ነፍሱም መልካምን ባትጠግብ መቃብርንም ባያገኝ፥ እኔ ስለ እርሱ። ከእርሱ ይልቅ ጭንጋፍ ይሻላል አልሁ።
4 ፤ በከንቱ መጥቶአል በጨለማ ይሄዳል ስሙም በጨለማ ይሸፈናል፤
5 ፤ ደግሞም ፀሐይን አላየውም አላወቀውምም፤ ለዚህም ከዚያ ይልቅ ዕረፍት አለው።
6 ፤ ሺህ ዓመት ሁለት ጊዜ በሕይወት ቢኖር መልካምንም ባያይ፥ ሁሉ ወደ አንድ ስፍራ የሚሄድ አይደለምን?
7 ፤ የሰው ድካም ሁሉ ለአፉ ነው፥ ነፍሱ ግን አትጠግብም።
8 ፤ ከሰነፍ ይልቅ ለጥበበኛ ጥቅም ምንድር ነው? በሕያዋን ፊትስ መሄድ ለሚያውቅ ለድሀ ጥቅሙ ምንድር ነው?
9 ፤ በዓይን ማየት በነፍስ ከመቅበዝበዝ ይሻላል፤ ይህም ደግሞ ከንቱ ነፋስንም እንደ መከተል ነው።
10 ፤ የሆነው ስሙ አስቀድሞ ተጠራ፥ ሰውም እንደ ሆነ ታወቀ፤ ከእርሱ ከሚበረታው ጋር ይፋረድ ዘንድ አይችልም።
11 ፤ ከንቱን የሚያበዛ ብዙ ነገር አለና ለሰው ጥቅሙ ምንድር ነው?
12 ፤ ሰው በከንቱ ወራቱ ቍጥርና እንደ ጥላ በሚያሳልፈው ዘመኑ በሕይወቱ ሳለ ለሰው የሚሻለውን የሚያውቅ ማነው? ወይስ ለሰው ከፀሐይ በታች ከእርሱ በኋላ የሚሆነውን ማን ይነግረዋል?