መጽሐፈ ነህምያ።

1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13


ምዕራፍ 5

በወንድሞቻቸውም በአይሁድ ላይ ትልቅ የሕዝቡና የሚስቶቻቸው ጩኸት ሆነ።
2 ፤ አያሌዎቹም። ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችን ብዙዎች ናቸው፤ በልተንም በሕይወት እንድንኖር እህልን እንሸምት ይሉ ነበር።
3 ፤ አያሌዎቹም። ከራብ የተነሣ እህልን እንሸምት ዘንድ እርሻችንና ወይናችንን ቤታችንንም አስይዘናል ይሉ ነበር።
4 ፤ ሌሎቹም። ለንጉሡ ግብር እርሻችንንና ወይናችንን አስይዘን ገንዘብ ተበድረናል፤
5 ፤ አሁንም ሥጋችን እንደ ወንድሞቻችን ሥጋ፥ ልጆቻችንም እንደ ልጆቻቸው ናቸው፤ እነሆም ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችን ባሪያዎች ይሆኑ ዘንድ ሰጥተናል፥ ከሴቶችም ልጆቻችን ባሪያዎች ሆነው የሚኖሩ አሉ፤ ታላላቆችም እርሻችንና ወይናችንን ይዘዋልና ልናድናቸው አንችልም ይሉ ነበር።
6 ፤ እኔም ጩኸታቸውንና ይህን ቃል በሰማሁ ጊዜ እጅግ ተቈጣሁ።
7 ፤ በልቤም አሰብሁ፥ ታላላቆቹንና ሹማምቱንም። ሁላችሁ እያንዳንዳችሁ ወለድ ትወስዳላችሁ ብዬ ተጣላኋቸው፤ ትልቅም ጉባኤ ሰበሰብሁባቸው።
8 ፤ እኔም። ለአሕዛብ የተሸጡትን ወንድሞቻችንን አይሁድን በፈቃዳችን ተቤዠን፤ እናንተስ ወንድሞቻችሁን ትሸጣላችሁን? እነርሱስ ለእኛ የተሸጡ ይሆናሉን? አልኋቸው። እነርሱም ዝም አሉ፥ መልስም አላገኙም።
9 ፤ ደግሞም አልሁ። የምታደርጉት ነገር መልካም አይደለም፤ ጠላቶቻችን አሕዛብ እንዳይሰድቡን አምላካችንን በመፍራት ትሄዱ ዘንድ አይገባችሁምን?
10 ፤ እኔም ደግሞ ወንድሞቼም ብላቴኖቼም ገንዘብና እህል ለእነርሱ አበድረናል፤ እባካችሁ፥ ይህን ወለድ እንተውላቸው።
11 ፤ እርሻቸውንና ወይናቸውን ወይራቸውንና ቤታቸውንም ከእነርሱም የወሰዳችሁትን ገንዘቡንና እህሉን፥ ወይን ጠጁንና ዘይቱን ከመቶ እጅ አንድ እጅ እባካችሁ ዛሬ መልሱላቸው።
12 ፤ እነርሱም። እንመልስላቸዋለን፥ ከእነርሱም ምንም አንሻም፤ እንደ ተናገርህ እንዲሁ እናደርጋለን አሉ። ካህናቱንም ጠርቼ እንደዚህ ነገር ያደርጉ ዘንድ አማልኋቸው።
13 ፤ ደግሞም ልብሴን አራገፍሁና። ይህን ነገር የማያደርገውን ሰው ከቤቱና ከሥራው እንዲሁ እግዚአብሔር ያራግፈው፤ እንዲሁም የተራገፈና ባዶ ይሁን አልሁ። ጉባኤውም ሁሉ። አሜን አሉ፥ እግዚአብሔርንም አመሰገኑ፤ ሕዝቡም እንደዚህ ነገር አደረጉ።
14 ፤ ንጉሡም በይሁዳ ምድር ላይ አለቃ እሆን ዘንድ ካዘዘኝ ጊዜ ጀምሮ ከንጉሡ ከአርጤክስስ ከሀያኛው ዓመት እስከ ሠላሳ ሁለተኛው ዓመት ድረስ አሥራ ሁለት ዓመት ያህል እኔና ወንድሞቼ ለአለቃ የሚገባውን ስንቅ አልበላንም።
15 ፤ ከእኔ አስቀድመው የነበሩት አለቆች ግን በሕዝቡ ላይ አክብደው ነበር፤ ስለ እንጀራውና ስለ ወይኑ አርባ ሰቅል ብር ይወስዱ ነበር፤ ሎሌዎቻቸውም ደግሞ በሕዝቡ ላይ ይሠለጥኑ ነበር፤ እኔ ግን እግዚአብሔርን ስለ ፈራሁ እንዲህ አላደረግሁም።
16 ፤ ደግሞም አጥብቄ የቅጥሩን ሥራ ሠራሁ፥ እርሻም አልገዛንም፤ ብላቴኖቼም ሁሉ ወደዚያው ወደ ሥራው ተሰበሰቡ።
17 ፤ ደግሞም በዙሪያችን ካሉት አሕዛብ ወደ እኛ ከመጡት ሌላ ከአይሁድና ከሹማምቱ መቶ አምሳ ሰዎች በገበታዬ ነበሩ።
18 ፤ ከወፎችም በቀር ለአንድ ቀን አንድ በሬና ስድስት የሰቡ በጎች፥ በአሥር በአሥር ቀንም ብዙ ልዩ ልዩ ዓይነት ወይን ጠጅ ይዘጋጅልኝ ነበር፤ ነገር ግን አገዛዝ በሕዝቡ ላይ ከብዶ ነበርና ለአለቃ የሚገባውን ስንቅ አልሻም ነበር።
19 ፤ አምላኬ ሆይ፥ ለዚህ ሕዝብ ያደረግሁትን ሁሉ ለበጎነት አስብልኝ።