መጽሐፈ ነህምያ።

1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13


ምዕራፍ 4

ሰንባላጥም ቅጥሩን እንደ ሠራን በሰማ ጊዜ እጅግ ተቈጣ፥ ተበሳጨም፥ በአይሁድም አላገጠ።
2 ፤ በወንድሞቹና በሰማርያ ሠራዊትም ፊት። እነዚህ ደካሞች አይሁድ የሚሠሩት ምንድር ነው? ይተዉላቸዋልን? ይሠዋሉን? በአንድ ቀንስ ይጨርሳሉን? የተቃጠለውንስ ድንጋይ ከፍርስራሹ መልሰው ያድኑታልን? ብሎ ተናገረ።
3 ፤ አሞናዊውም ጦብያ በአጠገቡ ቆሞ። በድንጋይ በሚሠሩት ቅጥራቸው ላይ ቀበሮ ቢመጣበት ያፈርሰዋል አለ።
4 ፤ አምላካችን ሆይ፥ ተንቀናልና ስማ፤ ስድባቸውን በራሳቸው ላይ መልስባቸው፤ በምርኮ አገር ለብዝበዛ አሳልፈህ ስጣቸው።
5 ፤ በደላቸውንም አትክደን፥ ኃጢአታቸውም ከፊትህ አይደምሰስ፤ በሠራተኞች ፊት አስቆጥተውሃልና።
6 ፤ ቅጥሩንም ሠራን፤ ቅጥሩም ሁሉ እስከ እኵሌታው ድረስ ተጋጠመ፤ የሕዝቡም ልብ ለሥራው ጨከነ።
7 ፤ ሰንባላጥና ጦብያም ዓረባውያንም አሞናውያንም አሽዶዳውያንም የኢየሩሳሌም ቅጥር እየታደሰ እንደ ሄደ፥ የፈረሰውም ሊጠገን እንደ ተጀመረ በሰሙ ጊዜ እጅግ ተቈጡ።
8 ፤ መጥተውም ኢየሩሳሌምን ይወጉና ያሸብሩ ዘንድ ሁሉም በአንድነት ተማማሉ።
9 ፤ ወደ አምላካችንም ጸለይን፥ ከእነርሱም የተነሣ በአንጻራቸው ተጠባባቂዎች በሌሊትና በቀን አደረግን።
10 ፤ ይሁዳም። የተሸካሚዎች ኃይል ደከመ፥ ፍርስራሹም ብዙ ነው፤ ቅጥሩንም እንሠራ ዘንድ አንችልም አሉ።
11 ፤ ጠላቶቻችንም። ወደ መካከላቸው እስክንመጣና እስክንገድላቸው ድረስ ሥራቸውንም እስክናስተጓጕል ድረስ አያውቁምና አያዩም አሉ።
12 ፤ በአጠገባቸውም የተቀመጡት አይሁድ መጥተው። ከስፍራው ሁሉ ይመጡብናል ብለው አሥር ጊዜ ነገሩን።
13 ፤ ከቅጥሩም በስተ ኋላ በኩል ባለው በታችኛው ስፍራ ሰይፋቸውን ጦራቸውንም ቀስታቸውንም አስይዤ ሕዝቡን በየወገናቸው አቆምኋቸው።
14 ፤ አይቼም ተነሣሁ፥ ታላላቆቹንና ሹማምቱንም የቀሩትንም ሕዝብ። አትፍሩአቸው፤ ታላቁንና የተፈራውን ጌታ አስቡ፥ ስለ ወንድሞቻችሁም ስለ ወንዶችና ስለ ሴቶች ልጆቻችሁም ስለ ሚስቶቻችሁም ስለ ቤቶቻችሁም ተዋጉ አልኋቸው።
15 ፤ ጠላቶቻችንም ይህ ነገር እንደ ደረሰልን፥ እግዚአብሔርም ምክራቸውን ከንቱ እንዳደረገው ሰሙ፤ እኛም ሁላችን ወደ ቅጥሩ እያንዳንዳችን ወደ ሥራችን ተመለስን።
16 ፤ ከዚያም ቀን ጀምሮ እኵሌቶቹ ብላቴኖቼ ሥራ ይሠሩ ነበር፥ እኵሌቶቹም ጋሻና ጦር ቀስትና ጥሩርም ይዘው ነበር፤ አለቆቹም ከይሁዳ ቤት ሁሉ በኋላ ይቆሙ ነበር።
17 ፤ ቅጥሩንም የሚሠሩትና ተሸካሚዎቹ በአንድ እጃቸው ይሠሩ ነበር፥ በአንድ እጃቸውም የጦር መሣሪያቸውን ይይዙ ነበር።
18 ፤ አናጢዎቹም ሁሉ እያንዳንዱ ሰይፉን በወገቡ ታጥቆ ይሠራ ነበር፤ ቀንደ መለከትም የሚነፋ በአጠገቤ ነበረ።
19 ፤ ታላላቆቹንና ሹማምቱን የቀሩትንም ሕዝብ። ሥራው ታላቅና ሰፊ ነው፥ እኛም በቅጥሩ ላይ ተበታትነናል፥ አንዱም ከሁለተኛው ርቆአል፤
20 ፤ የቀንደ መለከቱን ድምፅ ወደምትሰሙበት ስፍራ ወደዚያ ወደ እኛ ተሰብሰቡ፤ አምላካችን ስለ እኛ ይዋጋል አልኋቸው።
21 ፤ ሥራውንም ሠራን ከማለዳ ወገግታም ጀምሮ ከዋክብት እስኪወጡ ድረስ እኵሌቶቹ ጦር ይይዙ ነበር።
22 ፤ ደግሞም በዚያ ጊዜ ሕዝቡን። ሁላችሁ ከብላቴኖቻችሁ ጋር በኢየሩሳሌም ውስጥ እደሩ፤ በሌሊትም ጠባቂዎች ሁኑልን፥ በቀንም ሥሩ አልኋቸው።
23 ፤ እኔና ወንድሞቼም ብላቴኖቼም በኋላዬም የነበሩት ጠባቂዎች ልብሳችንን አናወልቅም ነበር።