መጽሐፈ ነህምያ።

1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13


ምዕራፍ 2

በንጉሡ በአርጤክስስ በሀያኛው ዓመት በኒሳን ወር የወይን ጠጅ በፊቱ በነበረ ጊዜ ጠጁን አንሥቼ ለንጉሡ ሰጠሁት። ቀድሞ ግን በፊቱ ያለ ኃዘን እኖር ነበር።
2 ፤ ንጉሡም። ሳትታመም ፊትህ ለምን አዘነ? ይህ የልብ ኅዘን ነው እንጂ ሌላ ነገር አይደለም አለኝ። እጅግም ብዙ አድርጌ ፈራሁ።
3 ፤ ንጉሡንም። ንጉሡ ሺህ ዓመት ይንገሥ፤ የአባቶቼ መቃብር ያለባት ከተማ ተፈትታለችና፥ በሮችዋም በእሳት ተቃጥለዋልና ፊቴ ስለ ምን አይዘን? አልሁት።
4 ፤ ንጉሡም። ምን ትለምነኛለህ? አለኝ። እኔም ወደ ሰማይ አምላክ ጸለይሁ።
5 ፤ ንጉሡንም። ንጉሡን ደስ ቢያሰኝህ፥ ባሪያህም በፊትህ ሞገስ ቢያገኝ፥ እሠራው ዘንድ ወደ ይሁዳ ወደ አባቶቼ መቃብር ከተማ ስደደኝ አልሁት።
6 ፤ ንግሥቲቱም በአጠገቡ ተቀምጣ ሳለች ንጉሡ። መንገድህ እስከ መቼ ድረስ ይሆናል? መቼስ ትመለሳለህ? አለኝ። ንጉሡም ይሰድደኝ ዘንድ ደስ አለው፤ እኔም ዘመኑን ቀጠርሁለት።
7 ፤ ንጉሡንም። ንጉሡ ደስ ቢለው፥ እስከ ይሁዳ አገር እንዲያደርሱኝ በወንዝ ማዶ ላሉት ገዦች ደብዳቤ ይሰጠኝ፤
8 ፤ በቤቱም አጠገብ ላለው ለግንብ በሮች፥ ለከተማውም ቅጥር፥ ለምገባበትም ቤት እንጨት እንዲሰጠኝ ለንጉሡ ዱር ጠባቂ ለአሳፍ ደብዳቤ ይሰጠኝ አልሁት። ንጉሡም በእኔ ላይ መልካም እንደ ሆነችው እንደ አምላኬ እጅ ሰጠኝ።
9 ፤ በወንዙም ማዶ ወዳሉት አለቆች መጥቼ የንጉሡን ደብዳቤ ሰጠኋቸው ንጉሡም ከእኔ ጋር የሠራዊቱን አለቆችና ፈረሰኞች ሰደደ።
10 ፤ ሖሮናዊውም ሰንባላጥና ባሪያው አሞናዊ ጦብያ ለእስራኤል ልጆች መልካምን ነገር የሚሻ ሰው እንደ መጣ በሰሙ ጊዜ እጅግ ተበሳጩ።
11 ፤ ወደ ኢየሩሳሌምም ደረስሁ፥ በዚያም ሦስት ቀን ያህል ተቀመጥሁ።
12 ፤ በሌሊትም ተነሣሁ፥ ከእኔም ጋር አያሌ ሰዎች ነበሩ፤ እግዚአብሔርም ለኢየሩሳሌም አደርገው ዘንድ በልቤ ያኖረውን ለማንም አላስታወቅሁም፤ ተቀምጬበት ከነበረው እንስሳ በቀር ከእኔ ጋር ምንም እንስሳ አልነበረም።
13 ፤ በሸለቆውም በር ወጣሁ፥ ወደ ዘንዶውም ምንጭና ወደ ጕድፍ መጣያው በር ሄድሁ፤ የፈረሰውንም የኢየሩሳሌምን ቅጥር፥ በእሳትም የተቃጠሉትን በሮችዋን ተመለከትሁ።
14 ፤ ወደ ምንጩም በርና ወደ ንጉሡ መዋኛ አለፍሁ፤ ተቀምጬበትም የነበረው እንስሳ የሚያልፍበት ስፍራ አልነበረም።
15 ፤ በሌሊትም በፈፋው በኩል ወጥቼ ቅጥሩን ተመለከትሁ፤ ዘወርም ብዬ በሸለቆው በር ገባሁ፥ እንዲሁም ተመለስሁ።
16 ፤ ሹማምቱ ግን ወዴት እንደ ሄድሁ፥ ምን እንዳደረግሁም አላወቁም ነበር፤ ለአይሁድና ለካህናቱ፥ ለታላላቆችና ለሹማምቱም፥ ሥራም ይሠሩ ለነበሩት ለሌሎች ገና አልተናገርሁም ነበር።
17 ፤ እኔም። እኛ ያለንበትን ጕስቍልና ኢየሩሳሌም እንደ ፈረሰች፥ በሮችዋም በእሳት እንደ ተቃጠሉ ታያላችሁ፤ አሁንም ከእንግዲህ ወዲህ መሳለቂያ እንዳንሆን ኑና የኢየሩሳሌምን ቅጥር እንሥራ አልኋቸው።
18 ፤ የአምላኬም እጅ በእኔ ላይ መልካም እንደሆነች፥ ንጉሡም የነገረኝን ቃል ነገርኋቸው። እነርሱም። እንነሣና እንሥራ አሉ። እጃቸውንም ለበጎ ሥራ አበረቱ።
19 ፤ ሖሮናዊውም ሰንባላጥ፥ ባሪያውም አሞናዊው ጦብያ፥ ዓረባዊውም ጌሳም በሰሙ ጊዜ በንቀት ሳቁብን፥ ቀላል አድርገውንም። ይህ የምታደርጉት ነገር ምንድር ነው? በውኑ በንጉሡ ላይ ትሸፍቱ ዘንድ ትወድዳላችሁን? አሉ።
20 ፤ እኔም መልሼ። የሰማይ አምላክ ያከናውንልናል፥ እኛም ባሪያዎቹ ተነሥተን እንሠራለን፤ እናንተ ግን በኢየሩሳሌም እድል ፈንታና መብት መታሰቢያም የላችሁም አልኋቸው።