ምዕራፍ 9

የይሩበኣል ልጅ አቤሜሌክም ወደ ሴኬም ወደ እናቱ ወንድሞች ሄደ፥ ለእነርሱም ለእናቱ አባት ቤተ ሰቦችም ሁሉ።
2 ፤ በሴኬም ሰዎች ሁሉ ጆሮ። ሰባ የሆኑት የይሩበኣል ልጆች ሁሉ ቢገዙአችሁ ወይስ አንድ ሰው ቢገዛችሁ ምን ይሻላችኋል? ብላችሁ ንገሩአቸው ብዬ እለምናችኋለሁ፤ ደግሞ እኔ የአጥንታችሁ ፍላጭ የሥጋችሁ ቍራጭ እንደ ሆንሁ አስቡ ብሎ ተናገራቸው።
3 ፤ የእናቱም ወንድሞች ይህን ቃል ሁሉ ስለ እርሱ በሴኬም ሰዎች ሁሉ ጆሮ ተናገሩ፤ እነርሱም። እርሱ ወንድማችን ነው ብለው አቤሜሌክን ለመከተል ልባቸውን አዘነበሉት።
4 ፤ ከበኣልብሪትም ቤት ሰባ ብር ሰጡት፤ በዚያም አቤሜሌክ ምናምንቴዎችንና ወሮበሎችን ቀጠረበት፥ እነርሱም ተከተሉት።
5 ፤ ወደ አባቱም ቤት ወደ ዖፍራ ሄደ፤ ሰባ የሆኑትን የይሩበኣልን ልጆች ወንድሞቹን በአንድ ድንጋይ ላይ አረዳቸው፤ ትንሹ የይሩበኣል ልጅ ኢዮአታም ግን ተሸሽጎ ነበርና ተረፈ።
6 ፤ የሴኬምም ሰዎች ሁሉ ቤትሚሎም ሁሉ ተሰበሰቡ፥ ሄደውም በሴኬም በዓምዱ አጠገብ ባለው በአድባሩ ዛፍ በታች አቤሜሌክን አነገሡ።
7 ፤ ይህንም ነገር ለኢዮአታም በነገሩት ጊዜ፥ ሄዶ በገሪዛን ተራራ ራስ ላይ ቆመ፥ ድምፁንም አንሥቶ ጮኸ፥ እንዲህም አላቸው። የሴኬም ሰዎች ሆይ፥ እግዚአብሔር እንዲሰማችሁ ስሙኝ።
8 ፤ አንድ ጊዜ ዛፎች በላያቸው ንጉሥ ሊያነግሡ ጌዱ፤ ወይራውንም። በእኛ ላይ ንገሥ አሉት።
9 ፤ ወይራው ግን። እግዚአብሔርና ሰዎች በእኔ የሚከበሩበትን ቅባቴን ትቼ በዛፎች ላይ እንድሰፍፍ ልሂድ? አላቸው።
10 ፤ ዛፎችም በለሱን። መጥተህ በላያችን ንገሥ አሉት።
11 ፤ በለሱ ግን። ጣፋጭነቴንና መልካሙን ፍሬዬን ትቼ በዛፎች ላይ እንድሰፍፍ ልሂድ? አላቸው።
12 ፤ ዛፎችም ውይኑን። መጥተህ በላያችን ንገሥ አሉት።
13 ፤ ወይኑም። እግዚአብሔርንና ሰውን ደስ የሚያሰኘውን የወይን ጠጄን ትቼ በዛፎች ላይ እንድሰፍፍ ልሂድ? አላቸው።
14 ፤ ዛፎችም ሁሉ እሾህን። መጥተህ በላያችን ንገሥ አሉት።
15 ፤ እሾሁም ዛፎችን። በእውነት እኔን በእናንተ ላይ ታነግሡኝ እንደ ሆነ ኑ ከጥላዬ በታች ተጠጉ። እንዲሁም ባይሆን እሳት ከእሾህ ይውጣ፥ የሊባኖስንም ዝግባ ያቃጥል አላቸው።
16 ፤ አሁን እንግዲህ አቤሜሌክን በማንገሣችሁ እውነትንና ቅንነትን አድርጋችሁ እንደ ሆነ፥ ለይሩበኣልም ለቤቱም በጎ አድርጋችሁ እንደ ሆነ፥ እንዳደረገውም መጠን ለእርሱ የተገባውን አድርጋችሁ እንደ ሆነ፥
17 ፤ አባቴ ስለ እናንተ ተጋድሎ ነበርና፥ ከምድያምም እጅ ሊያድናችሁ ነፍሱን ለሞት አሳልፎ ሰጥቶ ነበርና፥
18 ፤ እናንተም ዛሬ በአባቴ ቤት ተነሥታችኋልና፥ ሰባ የሆኑትን ልጆቹንም በአንድ ድንጋይ ላይ አርዳችኋልና፥ ወንድማችሁም ስለ ሆነ የባሪያይቱን ልጅ አቤሜሌክን በሴኬም ሰዎች ላይ አንግሣችኋልና፥
19 ፤ እንግዲህ ለይሩበኣልና ለቤቱ እውነትንና ቅንነትን ዛሬ አድርጋችሁ እንደ ሆነ፥ በአቤሜሌክ ደስ ይበላችሁ፥ እርሱ ደግሞ በእናንተ ደስ ይበለው፤
20 ፤ እንዲህ ባይሆን ግን ከአቤሜሌክ እሳት ይውጣ፥ የሴኬምንም ሰዎች ቤትሚሎንም ይብላ፤ ከሴኬምም ሰዎች ከቤትሚሎም እሳት ይውጣ፥ አቤሜሌክንም ይብላ።
21 ፤ ኢዮአታምም ሸሽቶ አመለጠ፥ ወንድሙንም አቤሜሌክን ፈርቶ ወደ ብኤር ሄደ፥ በዚያም ተቀመጠ።
22 ፤ አቤሜሌክም በእስራኤል ላይ ሦስት ዓመት ነገሠ።
23 ፤ እግዚአብሔር በአቤሜሌክና በሴኬም ሰዎች መካከል ክፉን መንፈስ ሰደደ፤ የሴኬምም ሰዎች በአቤሜሌክ ላይ ተንኰል አደረጉ።
24 ፤ ይህም የሆነው፥ በሰባ የይሩበኣል ልጆቹ ላይ የተደረገው ዓመፅ እንዲመጣ፥ ደማቸውም በገደላቸው በወንድማቸው በአቤሜሌክ ላይ፥ ወንድሞቹንም እንዲገድል እጆቹን ባጸኑአቸው በሴኬም ሰዎች ላይ እንዲሆን ነው።
25 ፤ የሴኬምም ሰዎች በተራሮች ራስ ላይ ድብቅ ጦር አደረጉ፥ መንገድ ተላላፊዎችንም ሁሉ ይዘርፉ ነበር፤ አቤሜሌክም ይህን ወሬ ሰማ።
26 ፤ የአቤድም ልጅ ገዓል ከወንድሞቹ ጋር መጥቶ ወደ ሴኬም ገባ፤ የሴኬምም ሰዎች ታመኑበት።
27 ፤ ወደ እርሻውም ወጡ ወይናቸውንም ለቀሙ፥ ጠመቁትም፥ የደስታም በዓል አደረጉ፤ ወደ አምላካቸውም ቤት ገቡ፥ በሉም ጠጡም፥ አቤሜሌክንም ሰደቡ።
28 ፤ የአቤድም ልጅ ገዓል። የምንገዛለት አቤሜሌክ ማን ነው? ሴኬምስ ምንድርነው? እርሱ የይሩብኣል ልጅ አይደለምን? ዜቡልም የእርሱ ሹም አይደለምን? ለሴኬም አባት ለኤሞር ሰዎች ተገዙ፤
29 ፤ ስለ ምንስ ለዚህ እንገዛለን? ይህ ሕዝብ ከእጄ በታች ቢሆን ኖሮ አቤሜሌክን አሳድደው ነበር አለ። አቤሜሌክንም። ሠራዊትህን አብዝተህ ና፥ ውጣ አለው።
30 ፤ የከተማይቱ ገዥ ዜቡልም የአቤድን ልጅ የገዓልን ቃል በሰማ ጊዜ እጅግ ተቈጣ።
31 ፤ እንዲህም ብሎ ወደ አቤሜሌክ በተንኰል መልክተኞች ላከ። እነሆ፥ የአቤድ ልጅ ገዓልና ወንድሞቹ ወደ ሴኬም መጥተዋል፥ በአንተም ላይ ከተማይቱን አሸፍተዋል።
32 ፤ አሁንም አንተና ከአንተ ጋር ያሉት ሕዝብ በሌሊት ተነሡ፥ በሜዳም ሸምቁ፤
33 ፤ ነገም ፀሐይ በወጣች ጊዜ ማልደህ ተነሣ፥ በከተማይቱም ላይ ውደቅባት፤ እነሆም፥ እርሱና ከእርሱ ጋር ያሉት ሕዝብ በአንተ ላይ በወጡ ጊዜ እጅህ እንዳገኘች አድርግበት።
34 ፤ አቤሜሌክና ከእርሱም ጋር ያሉ ሕዝብ ሁሉ በሌሊት ተነሡ፥ በሴኬምም አቅራቢያ በአራት ወገን ሸመቁበት።
35 ፤ የአቤድም ልጅ ገዓል ወጥቶ በከተማይቱ በር አደባባይ ቆመ፤ አቤሜሌክና ከእርሱ ጋር ያሉት ሕዝብ ከሸመቁበት ስፍራ ተነሱ።
36 ፤ ገዓልም ሕዝቡን ባየ ጊዜ ዜቡልን። እነሆ፥ ከተራሮች ራስ ሕዝብ ይወርዳል አለው። ዜቡልም። ሰዎች የሚመስለውን የተራሮችን ጥላ ታያለህ አለው።
37 ፤ ገዓልም ደግሞ። እነሆ፥ ሕዝብ በምድር መካከል ይወርዳል፤ አንድም ወገን በምዖንኒም በአድባሩ ዛፍ መንገድ ይመጣል ብሎ ተናገረ።
38 ፤ ዜቡልም። እንገዛለት ዘንድ አቤሜሌክ ማን ነው? ያልህበት አፍህ አሁን የት አለ? ይህ የናቅኸው ሕዝብ አይደለምን? አሁንም ወጥተህ ከእነርሱ ጋር ተዋጋ አለው።
39 ፤ ገዓልም በሴኬም ሰዎች ፊት ወጣ፥ ከአቤሜሌክም ጋር ተዋጋ።
40 ፤ አቤሜሌክም አሳደደው፤ በፊቱም ሸሸ፥ እስከ በሩም አደባባይ ድረስ ብዙዎች ተጐድተው ወደቁ።
41 ፤ አቤሜሌክም በአሩማ ተቀመጠ፤ ዜቡልም ገዓልንና ወንድሞቹን በሴኬም እንዳይኖሩ አሳደዳቸው።
42 ፤ በነጋውም ሕዝቡ ወደ እርሻ ወጡ፤ አቤሜሌክም ሰማ።
43 ፤ ሕዝቡንም ወስዶ በሦስት ወገን ከፈላቸው፥ በሜዳም ሸመቀ፤ ተመለከተም፥ እነሆም፥ ሕዝቡ ከከተማ ወጡ፥ ተነሣባቸውም መታቸውም።
44 ፤ አቤሜሌክም ከእርሱም ጋር ያሉት ወገኖች ተጣደፉ በከተማይቱም በር አደባባይ ቆሙ፤ ሁለቱም ወገኖች በእርሻው ውስጥ በነበሩት ሁሉ ላይ ሮጡባቸው፥ መቱአቸውም።
45 ፤ አቤሜሌክም በዚያ ቀን ሁሉ ከከተማይቱ ጋር ተዋጋ፤ ከተማይቱንም ይዞ በእርሷ የነበሩትን ሕዝብ ገደለ፤ ከተማይቱንም አፈረሰ፥ ጨውም ዘራባት።
46 ፤ በሴኬምም ግንብ ውስጥ የነበሩ ሰዎች ሁሉ ይህን በሰሙ ጊዜ ወደ ኤልብሪት ቤት ወደ ምሽጉ ውስጥ ገቡ።
47 ፤ አቤሜሌክም በሴኬም ግንብ ውስጥ ያሉ ሰዎች ሁሉ አንድ ሆነው እንደ ተሰበሰቡ ሰማ።
48 ፤ አቤሜሌክና ከእርሱ ጋር ያሉትም ሕዝብ ሁሉ ወደ ሰልሞን ተራራ ወጡ፤ አቤሜሌክም በእጁ መጥረቢያ ወስዶ የዛፉን ቅርንጫፍ ቈረጠ፥ አንሥቶም በጫንቃው ላይ አደረገው፤ ከእርሱም ጋር ለነበሩት ሕዝብ። እኔ ሳደርግ ያያችሁትን፥ እናንተም ፈጥናችሁ እኔ እንዳደረግሁ አድርጉ አላቸው።
49 ፤ ሕዝቡም ሁሉ እንዲሁ እያንዳንዳቸው የዛፉን ቅርንጫፎች ቈረጡ፥ አቤሜሌክንም ተከትለው በምሽጉ ዙሪያ አኖሩአቸው፥ ምሽጉንም በላያቸው አቃጠሉት፤ የሴኬምም ግንብ ሰዎች ሁሉ ደግሞ አንድ ሺህ የሚያህሉ ወንድና ሴት ሞቱ።
50 ፤ አቤሜሌክም ወደ ቴቤስ መጣ፥ ቴቤስንም ከብቦ ያዛት።
51 ፤ በከተማይቱም ውስጥ ብርቱ ግንብ ነበረ፥ የከተማይቱም ሰዎች ሁሉ፥ ወንዱና ሴቱ ሁሉ፥ ወደዚያ ሸሹ፤ ደጁንም በኋላቸው ዘጉ፥ ወደ ግንቡም ሰገነት ላይ ወጡ።
52 ፤ አቤሜሌክም ወደ ግንቡ ቀርቦ ይዋጋ ነበር፥ በእሳትም ሊያቃጥለው ወደ ግንቡ ደጅ ደረሰ።
53 ፤ አንዲትም ሴት በአቤሜሌክ ራስ ላይ የወፍጮ መጅ ጣለችበት፥ አናቱንም ሰበረችው።
54 ፤ እርሱም ፈጥኖ ጋሻ ዣግሬውን ጠርቶ። እኔን። ሴት ገደለችው እንዳይሉ ሰይፍህን መዝዘህ ግደለኝ አለው፤ ጕልማሳውም ወጋው፥ ሞተም።
55 ፤ የእስራኤልም ሰዎች አቤሜሌክ እንደ ሞተ ባዩ ጊዜ እያንዳንዱ ወደ ስፍራው ተመለሰ።
56 ፤ እንዲሁ ሰባ ወንድሞቹን በመግደል አቤሜሌክ በአባቱ ላይ ያደረገውን ክፋት እግዚአብሔር መለሰበት።
57 ፤ እግዚአብሔርም የሴኬምን ሰዎች ክፋት ሁሉ በራሳቸው ላይ መለሰባቸው፤ የይሩበኣልም ልጅ የኢዮአታም እርግማን ደረሰባቸው።