ምዕራፍ 19

በዚያም ዘመን በእስራኤል ዘንድ ንጉሥ በሌለበት ጊዜ በተራራማው በኤፍሬም አገር ማዶ የተቀመጠ ሌዋዊ ነበረ፤ ከቤተ ልሔምም ይሁዳ ቁባት አገባ።
2 ፤ ቁባቱም አመነዘረችበት፥ ትታውም ወደ አባትዋ ቤት ወደ ቤተ ልሔም ይሁዳ ሄደች፤ በዚያም አራት ወር ተቀመጠች።
3 ፤ ባልዋም ተነሣ፥ ከእርስዋም ዕርቅ ሽቶ ወደ ቤቱ ሊመልሳት ፍለጋዋን ተከትሎ ሄደ፤ ከእርሱም ጋር አንድ አሽከር ሁለትም አህዮች ነበሩ። እርስዋም ወደ አባትዋ ቤት አገባችው፤ አባትዋም ባየው ጊዜ ደስ ብሎት ተገናኘው።
4 ፤ የብላቴናይቱም አባት አማቱ የግድ አለ፥ በቤቱም ሦስት ቀን ተቀመጠ፤ በሉም፥ ጠጡም፥ በዚያም አደሩ።
5 ፤ በአራተኛውም ቀን ማልደው ተነሡ፥ እርሱም ለመሄድ ተነሣ፤ የብላቴናይቱም አባት አማቹን። ሰውነትህን በቍራሽ እንጀራ አበርታ፥ ከዚያም በኋላ ትሄዳለህ አለው።
6 ፤ ተቀመጡም በአንድ ላይም በሉ ጠጡም፤ የብላቴናይቱም አባት ሰውዮውን። ዛሬ ደግሞ ከዚህ ለማደር፥ እባክህ፥ ፍቀድ፥ ልብህንም ደስ ይበለው አለው።
7 ፤ ሰውዮውም ሊሄድ ተነሣ፤ አማቱ ግን የግድ አለው፥ ዳግመኛም በዚያ አደረ።
8 ፤ በአምስተኛውም ቀን ለመሄድ ማልዶ ተነሣ፤ የብላቴናይቱም አባት። እባክህ፥ ሰውነትህን አበርታ፥ ቀኑም እስኪዋገድ ድረስ ቆይ አለው። ሁለቱም በሉ።
9 ፤ ሰውዮውም ከቁባቱና ከአሽከሩ ጋር ለመሄድ በተነሣ ጊዜ የብላቴናይቱ አባት አማቱ። እነሆ፥ ቀኑ ተዋግዶአል፤ በዚህ እደሩ፤ እነሆ፥ ቀኑ ለማለፍ ተዋግዶአል፤ ልባችሁ ደስ እንዲለው በዚህ እደሩ፤ ነገም ወደ ቤታችሁ እንድትደርሱ ማልዳችሁ መንገዳችሁን ትሄዳላችሁ አለው።
10 ፤ ሰውዮው ግን በዚያ ሌሊት ለማደር አልፈቀደም፥ ተነሥቶም ሄደ፥ ኢየሩሳሌምም ወደ ተባለች ወደ ኢያቡስ ፊት ለፊት ደረሰ። ከእርሱም ጋር ሁለት የተጫኑ አህዮች ነበሩ፥ ቁባቱም ከእርሱ ጋር ነበረች።
11 ፤ ወደ ኢያቡስም በደረሱ ጊዜ መሸባቸው፥ አሽከሩም ጌታውን። ና፥ ወደዚህ ወደ ኢያቡሳውያን ከተማ፥ እባክህ፥ እናቅና፥ በእርስዋም እንደር አለው።
12 ፤ ጌታውም። ከእስራኤል ወገን ወዳልሆነች ወደ እንግዳ ከተማ አንገባም፤ እኛ ወደ ጊብዓ እንለፍ አለው።
13 ፤ አሽከሩንም። ና፥ ከእነዚህ ስፍራ ወደ አንዱ እንቅረብ፤ በጊብዓ ወይም በራማ እንደር አለው።
14 ፤ መንገዳቸውንም ይዘው ሄዱ፤ የብንያምም ነገድ በምትሆነው በጊብዓ አጠገብ ሳሉ ፀሐይ ገባችባቸው።
15 ፤ በጊብዓም ገብተው ያድሩ ዘንድ ወደዚያ አቀኑ። በገባም ጊዜ ሊያሳድራቸው ማንም በቤቱ አልተቀበላቸውምና በከተማው አደባባይ ተቀመጡ።
16 ፤ እነሆም፥ አንድ ሽማግሌ ከእርሻው ሥራ ወደ ማታ መጣ፤ ይህም ሰው ከተራራማው ከኤፍሬም አገር ነበረ በጊብዓም በእንግድነት ተቀምጦ ነበር፤ የዚያ አገር ሰዎች ግን ብንያማውያን ነበሩ።
17 ፤ ዓይኑንም አንሥቶ መንገደኛውን በከተማው አደባባይ አየ፤ ሽማግሌውም። ወዴት ትሄዳለህ? ከወዴትስ መጣህ? አለው።
18 ፤ እርሱም። እኛ ከቤተ ልሔም ይሁዳ ወደ ተራራማው ወደ ኤፍሬም አገር ማዶ እናልፋለን፤ እኔ ከዚያ ነኝ፥ ወደ ቤተ ልሔምም ይሁዳ ሄጄ ነበር፥ አሁንም ወደ እግዚአብሔር ቤት እሄዳለሁ፤ በቤቱም የሚያሳድረኝ አጣሁ፤
19 ፤ ለአህዮቻችን ገለባና ገፈራ አለን፤ ለእኔና ለገረድህ ከባሪያዎችህም ጋር ላለው አሽከር እንጀራና የወይን ጠጅ አለን፤ አንዳችም አላጣንም አለው።
20 ፤ ሽማግሌውም። ሰላም ከአንተ ጋር ይሁን፤ የምትሻውንም ሁሉ እኔ እሰጥሃለሁ፤ በአደባባይ ግን አትደር አለው።
21 ፤ ወደ ቤቱም አስገባው፥ ለአህዮቹም ገፈራ ጣለላቸው፤ እግራቸውንም ታጠቡ፥ በሉም ጠጡም።
22 ፤ ሰውነታቸውንም ደስ ባሰኙ ጊዜ ወስላቶች የሆኑ የከተማው ሰዎች ቤቱን ከበቡ በሩንም ይደበድቡ ነበር፤ ባለቤቱንም ሽማግሌውን። ወደ ቤትህ የገባውን ሰው እንድንደርስበት አውጣልን አሉት።
23 ፤ ባለቤቱም ሽማግሌው ወደ እነርሱ ወጥቶ። ወንድሞቼ ሆይ፥ ይህን ክፉ ነገር፥ እባካችሁ፥ አታድርጉ፤ ይህ ሰው ወደ ቤቴ ገብቶአልና እንደዚህ ያለ ኃጢአት አትሥሩ።
24 ፤ ድንግል ልጄና የእርሱም ቁባት፥ እነሆ፥ አሉ፥ አሁንም አወጣቸዋለሁ፤ አዋርዱአቸው እንደ ወደዳችሁም አድርጉባቸው፤ ነገር ግን በዚህ ሰው ላይ እንደዚህ ያለ ኃጢአት አታድርጉ አላቸው።
25 ፤ ሰዎቹ ግን ነገሩን አልሰሙም፤ ሰውዮውም ቁባቱን ይዞ አወጣላቸው፤ ደረሱባትም፥ ሌሊቱንም ሁሉ እስኪነጋ ድረስ አመነዘሩባት፤ ጎህ በቀደደም ጊዜ ለቀቁአት።
26 ፤ ሴቲቱም ማለዳ መጣች፥ ጌታዋም ባለበት በሰውዮው ቤት ደጅ ወድቃ እስኪነጋ ድረስ በዚያ ቀረች።
27 ፤ ጌታዋም ማለዳ ተነሣ የቤቱንም ደጅ ከፈተ፥ መንገዱንም ለመሄድ ወጣ፤ እነሆም ቁባቲቱ ሴት በቤቱ ደጃፍ ወድቃ፥ እጅዋም በመድረክ ላይ ነበረ።
28 ፤ እርሱም። ተነሺ፥ እንሂድ አላት፤ እርስዋ ግን ሞታ ነበርና አልመለሰችም፤ በዚያን ጊዜ በአህያው ላይ ጫናት፥ ተነሥቶም ወደ ስፍራው ሄደ።
29 ፤ ወደ ቤቱም በመጣ ጊዜ ካራ አነሣ፥ ቁባቱንም ይዞ ከአጥንቶችዋ መለያያ ላይ ለአሥራ ሁለት ቈራርጦ ወደ እስራኤል አገር ሁሉ ሰደደ።
30 ፤ ያየም ሁሉ። የእስራኤል ልጆች ከግብፅ ምድር ከወጡ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ እንዲህ ያለ ነገር ከቶ አልተደረገም፥ አልታየምም፤ አስቡት፥ በዚህም ተመካከሩ፥ ተነጋገሩም ይባባል ነበር።