ምዕራፍ 10

ከአቤሜሌክም በኋላ ከይሳኮር ነገድ የሆነ የዱዲ ልጅ የፎሖ ልጅ ቶላ እስራኤልን ለማዳን ተነሣ፤ በተራራማውም በኤፍሬም አገር ባለችው በሳምር ተቀምጦ ነበር።
2 ፤ በእስራኤልም ላይ ሀያ ሦስት ዓመት ፈረደ፤ ሞተም፥ በሳምርም ተቀበረ።
3 ፤ ከእርሱም በኋላ ገለዓዳዊው ኢያዕር ተነሣ፥ በእስራኤልም ላይ ሀያ ሁለት ዓመት ፈረደ።
4 ፤ በሠላሳ የአህያ ግልገሎች ይቀመጡ የነበሩ ሠላሳ ልጆችም ነበሩት፤ ለእነርሱም እስከ ዛሬ ድረስ የኢያዕር መንደሮች የተባሉ በገለዓድ ምድር ያሉ ሠላሳ ከተሞች ነበሩአቸው።
5 ፤ ኢያዕርም ሞተ፥ በቃሞንም ተቀበረ።
6 ፤ የእስራኤልም ልጆች በእግዚአብሔር ፊት እንደ ገና ክፉ ሥራ ሠሩ በኣሊምንና አስታሮትን የሶርያንም አማልክት፥ የሲዶናንም አማልክት፥ የሞዓብንም አማልክት፥ የአሞንንም ልጆች አማልክት፥ የፍልስጥኤማውያንንም አማልክት አመለኩ፤ እግዚአብሔርንም ተዉ፥ አላመለኩትምም።
7 ፤ የእግዚአብሔርም ቍጣ በእስራኤል ላይ ነደደ፥ በፍልስጥኤማውያንና በአሞን ልጆች እጅ አሳልፎ ሰጣቸው።
8 ፤ በዚያም ዓመት የእስራኤልን ልጆች ሥቃይ አበዙባቸው፤ በዮርዳኖስ ማዶ በአሞራውያን አገር በገለዓድ ውስጥ ያሉትን የእስራኤልን ልጆች ሁሉ አሥራ ስምንት ዓመት ተጋፉአቸው።
9 ፤ የአሞንም ልጆች ከይሁዳ ከብንያምና ከኤፍሬም ቤት ጋር ደግሞ ሊዋጋ ዮርዳኖስን ተሻገሩ፤ እስራኤልም እጅግ ተጨነቁ።
10 ፤ የእስራኤልም ልጆች። አምላካችንን ትተን በኣሊምን አምልከናልና አንተን በድለናል ብለው ወደ እግዚአብሔር ጮኹ።
11 ፤ እግዚአብሔርም የእስራኤልን ልጆች አላቸው። ግብፃውያን፥ አሞራውያንም፥ የአሞንም ልጆች፥
12 ፤ ፍልስጥኤማውያንም፥ ሲዶናውያንም፥ አማሌቃውያንም፥ ማዖናውያንም አላስጨነቋችሁምን? ወደ እኔም ጮኻችሁ፥ እኔም ከእጃቸው አዳንኋችሁ።
13 ፤ እናንተ ግን ተዋችሁኝ ሌሎችንም አማልክት አመለካችሁ፤ ስለዚህም ደግሞ አላድናችሁም።
14 ፤ ሄዳችሁም የመረጣችኋቸውን አማልክት ጥሩ፤ እነርሱም በመከራችሁ ጊዜ ያድኑአችሁ።
15 ፤ የእስራኤልም ልጆች እግዚአብሔርን። እኛ ኃጢአትን ሠርተናል፤ አንተ ደስ የሚያሰኝህን አድርግብን ዛሬ ግን፥ እባክህ፥ አድነን አሉት።
16 ፤ ሌሎችንም አማልክት ከመካከላቸው አስወገዱ፥ እግዚአብሔርንም አመለኩ፤ ነፍሱም ስለ እስራኤል ጕስቍልና አዘነች።
17 ፤ የአሞንም ልጆች ተሰብስበው በገለዓድ ሰፈሩ። የእስራኤልም ልጆች ተሰብስበው በምጽጳ ሰፈሩ።
18 ፤ ሕዝቡም፥ የገለዓድ አለቆች፥ እርስ በእርሳቸው። ከአሞን ልጆች ጋር መዋጋት የሚጀምር ማን ነው? እርሱ በገለዓድ ሰዎች ሁሉ ላይ አለቃ ይሆናል አሉ።