ምዕራፍ 15

ከዚህም በኋላ በስንዴ መከር ጊዜ ሶምሶን የፍየል ጠቦት ይዞ ሚስቱን ሊጠይቅ ሄደና። ወደ ጫጉላ ቤት ወደ ሚስቴ ልግባ አለ፤ አባትዋ ግን እንዳይገባ ከለከለው።
2 ፤ አባትዋም። ፈጽመህ የጠላሃት መስሎኝ ለሚዜህ አጋባኋፅት፤ ታናሽ እኅትዋ ከርስዋ ይልቅ የተዋበች አይደለችምን? እባክህ፥ በእርስዋ ፋንታ አግባት አለው።
3 ፤ ሶምሶንም። ከእንግዲህ ወዲህ በፍልስጥኤማውያን ላይ ክፉ ባደርግ እኔ ንጹሕ ነኝ አላቸው።
4 ፤ ሶምሶንም ሄዶ ሦስት መቶ ቀበሮች ያዘ፤ ችቦም ወስዶ ሁለት ሁለቱንም ቀበሮዎች በጅራታቸው አሰረ፥ በሁለቱም ጅራቶች ማካከል አንድ ችቦ አደረገ።
5 ፤ ችቦውንም አንድዶ በቆመው በፍልስጥኤማውያን እህል መካከል ሰደዳቸው፤ ነዶውንም የቆመውንም እህል ወይኑንም ወይራውንም አቃጠለ።
6 ፤ ፍልስጥኤማውያንም። ይህን ያደረገው ማን ነው? አሉ። እነርሱም። ሚስቱን ወስዶ ለሚዜው አጋብቶበታልና የተምናዊው አማች ሶምሶን ነው አሉ። ፍልስጥኤማያንም ወጥተው ሴቲቱንና አባትዋን በእሳት አቃጠሉ።
7 ፤ ሶምሶንም። እናንተ እንዲሁ ብታደርጉ እኔ እበቀላችኋለሁ፥ ከዚያም በኋላ ዐርፋለሁ አላቸው።
8 ፤ እርሱም ጭን ጭናቸውን ብሎ በታላቅ አገዳደል መታቸው፤ ወርዶም በኤጣም ዓለት ባለው ዋሻ ውስጥ ተቀመጠ።
9 ፤ ፍልስጥኤማውያንም ወጡ፥ በይሁዳም ሰፈሩ፥ በሌሒ ላይም ተበታትነው ተቀመጡ።
10 ፤ የይሁዳም ሰዎች። በእኛ ላይ የወጣችሁት ለምንድር ነው? አሉ። እነርሱም። ሶምሶንን ልናስር፥ እንዳደረገብንም ልናደርግበት መጥተናል አሉ።
11 ፤ ከይሁዳም ሰዎች ሦስት ሺህ የሚያህሉ በኤጣም ዓለት ወዳለው ዋሻ ወርደው ሶምሶንን። ገዦቻችን ፍልስጥኤማውያን እንደ ሆኑ አታውቅምን? ያደረግህብን ይህ ምንድር ነው? አሉት። እርሱም። እንዳደረጉብኝ እንዲሁ አደረግሁባቸው አላቸው።
12 ፤ እነርሱም። አስረን በፍልስጥኤማውያን እጅ አሳልፈን ልንሰጥህ መጥተናል አሉት። ሶምሶንም። እናንተ እንዳትገድሉኝ ማሉልኝ አላቸው።
13 ፤ እነርሱም። አስረን በእጃቸው አሳልፈን እንሰጥሃለን እንጂ አንገድልህም ብለው ተናገሩት። በሁለትም አዲስ ገመድ አስረው ከዓለቱ ውስጥ አወጡት።
14 ፤ ወደ ሌሒ በመጣ ጊዜም ፍልስጥኤማውያን እልል እያሉ ተገናኙት። የእግዚአብሔርም መንፈስ በኃይል ወረደበት፤ ክንዱም የታሰረበት ገመድ በእሳት እንደ ተበላ እንደ ተልባ እግር ፈትል ሆነ፥ ማሰሪያዎቹም ከእጁ ወደቁ።
15 ፤ አዲስም የአህያ መንጋጋ አገኘ፥ እጁንም ዘርግቶ ወሰደው፥ በእርሱም አንድ ሺህ ሰው ገደለ።
16 ፤ ሶምሶንም። በአህያ መንጋጋ ክምር በክምር ላይ አድርጌአቸዋለሁ፤ በአህያ መንጋጋ አንድ ሺህ ሰው ገድያለሁ አለ።
17 ፤ መናገሩንም በፈጸመ ጊዜ መንጋጋውን ከእጁ ጣለ፤ የዚያንም ስፍራ ስም ራማትሌሒ ብሎ ጠራው።
18 ፤ እርሱም እጅግ ተጠምቶ ነበርና። አንተ ይህችን ታላቅ ማዳን በባሪያህ እጅ ሰጥተሃል፤ አሁንም በጥም እሞታለሁ፥ ባልተገረዙትም እጅ እወድቃለሁ ብሎ ወደ እግዚአብሔር ጮኸ።
19 ፤ እግዚአብሔርም በሌሒ ያለውን አዘቅት ሰነጠቀ፥ ከእርሱም ውኃ ወጣ፤ እርሱም ጠጣ፥ ነፍሱም ተመለሰች፥ ተጠናከረም። ስለዚህም የዚያን ቦታ ስም ዓይንሀቆሬ ብሎ ጠራው፤ ይህም እስከ ዛሬ ድረስ በሌሒ አለ።
20 ፤ በፍልስጥኤማውያንም ዘመን በእስራኤል ላይ ሀያ ዓመት ፈረደ።