ሰቆቃው ኤርምያስ

1 2 3 4 5


ምዕራፍ 4

አሌፍ። ወርቁ እንዴት ደበሰ! ጥሩው ወርቅ እንዴት ተለወጠ! የመቅደሱ ድንጋዮች በጐዳና ሁሉ ራስ ተበተኑ።
2 ፤ ቤት። ጥሩ ወርቅ የሚመስሉ የከበሩ የጽዮን ልጆች፥ የሸክላ ሠሪ እጅ እንደ ሠራው እንደ ሸክላ ዕቃ እንዴት ተቈጠሩ!
3 ፤ ጋሜል። ቀበሮች እንኳ ጡቶታቸውን ገልጠው ግልገሎቻቸውን አጠቡ፤ የወገኔ ልጅ ግን እንደ ምድረ በዳ ሰጐን ጨካኝ ሆነች።
4 ፤ ዳሌጥ። ጡት የሚጠባው የሕፃን ምላስ ከጥም የተነሣ ወደ ትናጋው ተጣበቀ፤ ሕፃናት እንጀራ ለመኑ፥ የሚቈርስላቸውም የለም።
5 ፤ ሄ። የጣፈጠ ነገር ይበሉ የነበሩ በመንገድ ጠፉ፤ በቀይ ግምጃ ያድጉ የነበሩ የፍግ ክምር አቀፉ።
6 ፤ ዋው። የማንም እጅ ሳይወድቅባት ድንገት ከተገለበጠች ከሰዶም ኃጢአት ይልቅ የወገኔ ሴት ልጅ ኃጢአት በዛች።
7 ፤ ዛይ። አለቆችዋ ከበረዶ ይልቅ ጥሩ፥ ከወተት ይልቅ ነጭ ነበሩ፤ ገላቸው ከቀይ ዕንቍ ይልቅ ቀይ ነበረ፥ መልካቸውም እንደ ሰንፔር ነበረ።
8 ፤ ሔት። ፊታቸው ከጥቀርሻ ይልቅ ጠቍሮአል፥ በመንገድም አልታወቁም፤ ቁርበታቸው ወደ አጥንታቸው ተጣብቆአል፤ ደርቆአል፤ እንደ እንጨት ሆኖአል።
9 ፤ ጤት። በሰይፍ የሞቱ በራብ ከሞቱት ይሻላሉ፤ እነዚህ የምድርን ፍሬ አጥተው ተወግተውም ቀጥነዋል።
10 ፤ ዮድ። የርኅሩኆች ሴቶች እጆች ልጆቻችውን ቀቅለዋል፤ የወገኔ ሴት ልጅ በመቀጥቀጥዋ መብል ሆኑአቸው።
11 ፤ ካፍ። እግዚአብሔር መዓቱን ፈጽሞአል፥ ጽኑ ቍጣውን አፍስሶአል፤ እሳትን በጽዮን ውስጥ አቃጠለ፥ መሠረትዋንም በላች።
12 ፤ ላሜድ። የምድር ነገሥታት በዓለምም የሚኖሩ ሁሉ አስጨናቂና ጠላት በኢየሩሳሌም በር እንዲገባ አላመኑም።
13 ፤ ሜም። የጻድቃንን ደም በውስጥዋ ስላፈሰሱ ስለ ነቢያቶችዋ ኃጢአትና ስለ ካህናቶች በደል ነው።
14 ፤ ኖን። ታውረው በመንገድ ላይ ተቅበዘበዙ፤ ልብሳቸው እንዳይዳሰስ በደም ረክሰዋል።
15 ፤ ሳምኬት። እናንተ ርኩሳን፥ ራቁ፥ ርቃችሁም ሂዱ፥ አትንኩ ብለው ጮኹባቸው። በሸሹና በተቅበዘበዙ ጊዜ፥ በአሕዛብ መካከል። በዚህ ከእንግዲህ ወዲህ አይኖሩም ተባለ።
16 ፤ ዔ። የእግዚአብሔር ፊት በተናቸው እርሱም ከእንግዲህ ወዲህ አይመለከታቸውም፤ የካህናቱን ፊት አላፈሩም፥ ሽማግሌዎቹንም አላከበሩም።
17 ፤ ፌ። ዓይናችን ወደ ከንቱ ረዳታችን ገና ሲመለከት ጠፍቶአል፤ በመቆየታችን ማዳን የማይቻለውን ሕዝብ ጠብቀናል።
18 ፤ ጻዴ። በአደባባያችን እንዳንሄድ ፍለጋችንን ተከተሉ፤ ፍጻሜያችን ቀርቦአል፥ ዕድሜያችን አልቆአል፥ ፍጻሜያችን ደርሶአል።
19 ፤ ቆፍ። አሳዳጆቻችን ከሰማይ ንስር ይልቅ ፈጣኖች ሆኑ፤ በተራሮች ላይ አሳደዱን፥ በምድረ በዳ ሸመቁብን።
20 ፤ ሬስ። ስለ እርሱ። በአሕዛብ መካከል በጥላው በሕይወት እንኖራለን ያልነው በእግዚአብሔር የተቀባ፥ የሕይወታችን እስትንፋስ፥ በጕድጓዳቸው ተያዘ።
21 ፤ ሳን። በዖፅ ምድር የምትኖሪ የኤዶምያስ ልጅ ሆይ፥ ደስ ይበልሽ ሐሤትም አድርጊ፤ ጽዋው ደግሞ ወደ አንቺ ያልፋል፥ አንቺም ትሰክሪአለሽ ትራቈቻለሽም።
22 ፤ ታው። የጽዮን ልጅ ሆይ፥ የበደልሽ ቅጣት ተፈጸመ፤ ከእንግዲህ ወዲህ አያስማርክሽም። የኤዶምያስ ልጅ ሆይ፥ በደልሽን ይቀጣል፤ ኃጢአትሽን ይገልጣል።