ሰቆቃው ኤርምያስ

1 2 3 4 5


ምዕራፍ 2

አሌፍ። ጌታ በቍጣው የጽዮንን ሴት ልጅ እንደ ምን አደመናት! የእስራኤልን ውበት ከሰማይ ወደ ምድር ጣለ፥ በቍጣውም ቀን የእግሩን መረገጫ አላሰበም።
2 ፤ ቤት። ጌታ የያዕቆብን ማደሪያዎች ሁሉ ዋጠ፥ አልራራምም፤ በመዓቱ የይሁዳን ሴት ልጅ አምቦች አፈረሰ፥ ወደ ምድርም አወረዳቸው፤ መንግሥቱንና አለቆችዋን አረከሰ።
3 ፤ ጋሜል። በጽኑ ቍጣው የእስራኤልን ቀንድ ሁሉ ቀጠቀጠ፤ ቀኝ እጁን ከጠላት ፊት ወደ ኋላ መለሰ፥ በዙሪያውም እንደሚባላ እንደ እሳት ነበልባል ያዕቆብን አቃጠለ።
4 ፤ ዳሌጥ። ቀስቱን እንደ ጠላት ገተረ፥ እንደ አስጨናቂ ቀኝ እጁን አጸና፥ ለዓይንም የሚያምረውን ሁሉ ገደለ፤ በጽዮን ሴት ልጅ ድንኳን መዓቱን እንደ እሳት አፈሰሰ።
5 ፤ ሄ። ጌታ እንደ ጠላት ሆነ፥ እስራኤልን ዋጠ፤ አዳራሾችዋን ሁሉ ዋጠ፥ አምቦችዋን አጠፋ፤ በይሁዳም ሴት ልጅ ኀዘንና ልቅሶ አበዛ።
6 ፤ ዋው። ማደሪያውን እንደ አትክልት ነቀለ፤ የበዓሉን ስፍራ አጠፋ፤ እግዚአብሔር በጽዮን ዓመት በዓሉንና ሰንበቱን አስረሳ፥ በቍጣውም መዓት ንጉሡንና ካህኑን አቃለለ።
7 ፤ ዛይ። ጌታ መሠዊያውን ጣለ፥ መቅደሱን ጠላ፥ የአዳራሾችዋንም ቅጥር በጠላት እጅ አሳልፎ ሰጠ፤ ድምፃቸውን እንደ ዓመት በዓል ቀን በእግዚአብሔር ቤት ከፍ ከፍ አደረጉ።
8 ፤ ሔት። እግዚአብሔር የጽዮንን ሴት ልጅ ቅጥር ያፈርስ ዘንድ አሰበ፤ የመለኪያውን ገመድ ዘረጋ፥ እጁን ከማጥፋት አልመለሰም፤ ምሽጉና ቅጥሩ እንዲያለቅሱ አደረገ፤ በአንድነት ደከሙ።
9 ፤ ጤት። በሮችዋ በመሬት ውስጥ ሰጠሙ፥ መወርወሪያዎችዋን አጠፋ ሰበረም፤ ንጉሥዋና አለቆችዋ ሕግ በሌለባቸው በአሕዛብ መካከል አሉ፤ ነቢያቶቻዋም ከእግዚአብሔር ዘንድ ራእይ አላገኙም።
10 ፤ ዮድ። የጽዮን ሴት ልጅ ሽማግሌዎች ዝም ብለው በመሬት ላይ ተቀምጠዋል፤ ትቢያን በራሳቸው ላይ ነሰነሱ፥ ማቅም ታጠቁ፤ የኢየሩሳሌም ደናግል ራሳቸውን ወደ ምድር አዘነበሉ።
11 ፤ ካፍ። ሕፃኑና ጡት የሚጠባው በከተማይቱ ጐዳና ላይ ሲዝሉ፥ ዓይኔ በእንባ ደከመች፥ አንጀቴም ታወከ፤ ስለ ወገኔ ሴት ልጅ ቅጥቃጤ ጉበቴ በምድር ላይ ተዘረገፈ።
12 ፤ ላሜድ። በከተማ ጐዳና እንደ ተወጋ ሰው በዛሉ ጊዜ፥ ነፍሳቸውም በእናቶቻቸው ብብት በወጣች ጊዜ፥ እናቶቻቸውን። እህልና የወይን ጠጅ ወዴት አለ? ይሉአቸዋል።
13 ፤ ሜም። የኢየሩሳሌም ሴት ልጅ ሆይ፥ ምን እመሰክርልሻለሁ? በምንስ እመስልሻለሁ? ድንግሊቱ የጽዮን ልጅ ሆይ፥ አጽናናሽ ዘንድ በምን አስተካክልሻለሁ? ስብራትሽ እንደ ባሕር ታላቅ ነውና፤ የሚፈውስሽ ማን ነው?
14 ፤ ኖን። ነቢያቶችሽ ከንቱና ሐሰተኛ ራእይ አይተውልሻል፤ ምርኮሽንም ይመልሱ ዘንድ በደልሽን አልገለጡም፤ ከንቱና የማይረባ ነገርንም አይተውልሻል።
15 ፤ ሳምኬት። መንገድ አላፊዎች ሁሉ እጃቸውን ያጨበጭቡብሻልና። በውኑ የውበት ፍጻሜና የምድር ሁሉ ደስታ የሚሉአት ከተማ ይህች ናትን? እያሉ፥ በኢየሩሳሌም ሴት ልጅ ላይ ያፍዋጫሉ፥ ራሳቸውንም ያነቃንቃሉ።
16 ፤ ዔ። ጠላቶችሽ ሁሉ አፋቸውን አላቀቁብሽ፤ እያፍዋጩና ጥርሳቸውን እያፋጩ። ውጠናታል፤ ነገር ግን ተስፋ ያደረግናት ቀን ይህች ናት፤ አግኝተናታል አይተናትማል ይላሉ።
17 ፤ ፌ። እግዚአብሔር ያሰበውን አደረገ፤ በቀድሞ ዘመን ያዘዘውን ቃል ፈጸመ፤ አፈረሰ አልራራምም፤ ጠላትንም ደስ አሰኘብሽ፥ የሚያስጨንቁሽንም ቀንድ ከፍ ከፍ አደረገ።
18 ፤ ጻዴ። ልባቸው ወደ ጌታ ጮኸ። የጽዮን ሴት ልጅ ቅጥር ሆይ፥ እንባሽን እንደ ፈሳሽ ቀንና ሌሊት አፍስሺ፤ ለሰውነትሽ ዕረፍት አትስጪ፤ የዓይንሽ ብሌን አታቋርጥ።
19 ፤ ቆፍ። ተነሺ፥ በሌሊት በመጀመሪያ ክፍል ጩኺ፥ በጌታም ፊት ልብሽን እንደ ውኃ አፍስሺ፤ በጐዳና ሁሉ ራስ ላይ በራብ ስለ ደከሙ ስለ ሕፃናትሽ ነፍስ እጆችሽን ወደ እርሱ አንሺ።
20 ፤ ሬስ። አቤቱ፥ እይ፤ በማን ላይ እንደዚህ እንዳደረግህ ተመልከት። በውኑ ሴቶች ፍሬያቸውን፥ ያቀማጠሉአቸውን ሕፃናት፥ ይበላሉን? በውኑ ካህኑና ነቢዩ በጌታ መቅደስ ውስጥ ይገደላሉን?
21 ፤ ሳን። ብላቴናውና ሽማግሌው በመንገዶች ላይ ተጋደሙ፤ ደናግሎቼና ጐበዛዝቴ በሰይፍ ወድቀዋል፤ በቍጣህ ቀን ገደልሃቸው፤ ሳትራራ አረድሃቸው።
22 ፤ ታው። እንደ በዓል ቀን የሚያስፈሩኝን ከዙሪያዬ ጠራህ፥ በእግዚአብሔር ቍጣ ቀንም ያመለጠ ወይም የቀረ አልተገኘም፤ ያቀማጠልኋቸውንና ያሳደግኋቸውን ጠላቴ በላቸው።