ሰቆቃው ኤርምያስ

1 2 3 4 5


ምዕራፍ 3

አሌፍ። በቍጣው በትር መከራ ያየ ሰው እኔ ነኝ።
2 ፤ ብርሃን ወደ ሌለበት ወደ ጨለማ መርቶ ወሰደኝ።
3 ፤ ዘወትር ቀኑን ሁሉ እጁን በላዬ መለሰ።
4 ፤ ቤት። ሥጋዬንና ቁርበቴን አስረጀ፥ አጥንቴን ሰበረ።
5 ፤ ቅጥር ሠራብኝ በሐሞትና በድካምም ከበበኝ።
6 ፤ ቀድሞ ሞተው እንደ ነበሩ በጨለማ አኖረኝ።
7 ፤ ጋሜል። እንዳልወጣ በዙሪያዬ ቅጥር ሠራብኝ፤ ሰንሰለቴን አከበደ።
8 ፤ በጠራሁና በጮኽሁ ጊዜ ጸሎቴን ከለከለ።
9 ፤ መንገዴን በተጠረበ ድንጋይ ዘጋ፥ ጐዳናዬንም አጣመመ።
10 ፤ ዳሌጥ። እንደሚሸምቅ ድብ እንደ ተሸሸገም አንበሳ ሆነብኝ።
11 ፤ መንገዴን ለወጠ፥ ገነጣጠለኝም፤ ባድማ አደረገኝ።
12 ፤ ቀስቱን ገተረ ለፍላጻውም እንደ ጊጤ አደረገኝ።
13 ፤ ሄ። የሰገባውን ፍላጻዎች በኵላሊቴ ውስጥ ተከለ።
14 ፤ ለወገኔ ሁሉ ማላገጫ ቀኑንም ሁሉ መሳለቂያ ሆንሁ።
15 ፤ ምሬት ሞላብኝ በእሬትም አጠገበኝ።
16 ፤ ዋው። ጥርሴን በጭንጫ ሰበረ፥ በአመድም ከደነኝ።
17 ፤ ነፍሴን ከሰላም አራቅህ፤ በጎ ነገርን ረሳሁ።
18 ፤ እኔም። ኃይሌ ከእግዚአብሔርም ዘንድ ያለው ተስፋዬ ጠፋ አልሁ።
19 ፤ ዛይ። መከራዬንና ችግሬን እሬትንና ሐሞትን አስብ።
20 ፤ ነፍሴ እያሰበችው በውስጤ ፈዘዘች።
21 ፤ ይህችን በልቤ አኖራለሁ፥ ስለዚህ እታገሣለሁ።
22 ፤ ሔት። ያልጠፋነው ከእግዚአብሔር ምሕረት የተነሣ ነው፤ ርኅራኄው አያልቅምና።
23 ፤ ማለዳ ማለዳ አዲስ ነው፤ ታማኝነትህ ብዙ ነው።
24 ፤ ነፍሴ። እግዚአብሔር እድል ፈንታዬ ነው፤ ስለዚህ ተስፋ አደርገዋለሁ አለች።
25 ፤ ጤት። እግዚአብሔር በተስፋ ለሚጠብቁት ለምትሻውም ነፍስ መልካም ነው።
26 ፤ ሰው ዝም ብሎ የእግዚአብሔርን ማዳን ተስፋ ቢያደርግ መልካም ነው።
27 ፤ ሰው በታናሽነቱ ቀንበር ቢሸከም መልካም ነው።
28 ፤ ዮድ። እርሱ አሸክሞታልና ዝም ብሎ ለብቻው ይቀመጥ።
29 ፤ ተስፋ የሆነው እንደ ሆነ አፉን በአፈር ውስጥ ያኑር።
30 ፤ ጕንጩን ለሚመታው ይስጥ፥ ስድብንም ይጥገብ።
31 ፤ ካፍ። ጌታ ለዘላለም አይጥልምና፤
32 ፤ ቢያሳዝንም እንደ ምሕረቱ ብዛት ይራራልና፤
33 ፤ የሰውን ልጆች ከልቡ አያስጨንቅም፥ አያሳዝንምም።
34 ፤ ላሜድ። በምድር የተጋዙትን ሁሉ ከእግሩ በታች ይረግጣቸው ዘንድ፥
35 ፤ የሰውን ፍርድ በልዑል ፊት ይመልስ ዘንድ፥
36 ፤ የሰውን ፍርድ ያጣምም ዘንድ ጌታ እሺ አይልም።
37 ፤ ሜም። ጌታ ያላዘዘውን የሚልና የሚፈጽም ማን ነው?
38 ፤ ከልዑል አፍ ክፉና መልካም ነገር አይወጣምን?
39 ፤ ሕያው ሰው የሚያጕረመርም፥ ሰው ስለ ኃጢአቱ ቅጣት የሚያጕረመርም ስለ ምንድር ነው?
40 ፤ ኖን። መንገዳችንን እንመርምርና እንፈትን፥ ወደ እግዚአብሔርም እንመለስ።
41 ፤ ልባችንን ከእጃችን ጋር በሰማይ ወዳለው ወደ እግዚአብሔር እናንሣ።
42 ፤ በድለናል ዐምፀናልም፥ አንተም ይቅር አላልህም።
43 ፤ ሳምኬት። በቍጣ ከደንኸን አሳደድኸንም፤ ገደልኸን፥ አልራራህም።
44 ፤ ጸሎት እንዳያልፍ ራስህን በደመና ከደንህ።
45 ፤ በአሕዛብ መካከል ጕድፍና ውዳቂ አደረግኸን።
46 ፤ ዔ። ጠላቶቻችን ሁሉ አፋቸውን ኣላቀቁብን።
47 ፤ ድንጋጤና ቍጣ፥ ጥፋትና ቅጥቃጤ ሆነብን።
48 ፤ ስለ ወገኔ ሴት ልጅ ቅጥቃጤ ዓይኔ የውኃ ፈሳሽ አፈሰሰች።
49
50 ፤ ፌ። እግዚአብሔር ከሰማይ እስኪጐበኝና እስኪመለከት ድረስ ዓይኔ ሳታቋርጥ ዝም ሳትል እንባ ታፈስሳለች።
51 ፤ ስለ ከተማዬ ቈነጃጅት ሁሉ ዓይኔ ነፍሴን አሳዘነች።
52 ፤ ጻዴ። በከንቱ ነገር ጠላቶች የሆኑኝ እንደ ወፍ ማደንን አደኑኝ።
53 ፤ ሕይወቴን በጕድጓድ አጠፉ፥ በላዬም ድንጋይ ጣሉ።
54 ፤ በራሴ ላይ ውኆች ተከነበሉ፤ እኔም። ጠፋሁ ብዬ ነበር።
55 ፤ ቆፍ። አቤቱ፥ በጠለቀ ጕድጓድ ውስጥ ሆኜ ስምህን ጠራሁ።
56 ፤ ድምፄን ሰማህ፤ ጆሮህን ከልመናዬ አትመልስ።
57 ፤ በጠራሁህ ቀን ቀርበህ። አትፍራ አልህ።
58 ፤ ሬስ። ጌታ ሆይ፥ ስለ ነፍሴ ተምዋግተህ ሕይወቴን ተቤዠህ።
59 ፤ አቤቱ፥ ጭንቀቴን አይተሃል፥ ፍርዴን ፍረድልኝ።
60 ፤ በቀላቸውን ሁሉና በእኔ ላይ ያለውን አሳባቸውን ሁሉ አየህ።
61 ፤ ሳን። አቤቱ፥ ስድባቸውንና በእኔ ላይ ያለውን አሳባቸውን ሁሉ፥
62 ፤ የተነሡብኝን ሰዎች ከንፈሮች ቀኑንም ሁሉ ያሰቡብኝን አሳባቸውን ሰማህ።
63 ፤ መቀመጣቸውንና መነሣታቸውን ተመልከት፤ እኔ መሳለቂያቸው ነኝ።
64 ፤ ታው። አቤቱ፥ እንደ እጃቸው ሥራ ፍዳቸውን ትከፍላቸዋለህ።
65 ፤ የልብ ዕውርነትንና እርግማንህን ትሰጣቸዋለህ።
66 ፤ አቤቱ፥ በቍጣ ታሳድዳቸዋለህ ከሰማይም በታች ታጠፋቸዋለህ።