መጽሐፈ አስቴር።

1 2 3 4 5 6 7 8 9 10


ምዕራፍ 7

ንጉሡና ሐማም ከንግሥቲቱ ከአስቴር ጋር ለመጠጣት መጡ።
2 ፤ በሁለተኛውም ቀን ንጉሡ በወይኑ ጠጅ ግብዣ ሳለ አስቴርን። ንግሥት አስቴር ሆይ፥ የምትለምኚኝ ምንድር ነው? ይሰጥሻል፤ የምትሺውስ ምንድር ነው? እስከ መንግሥቴ እኵሌታ እንኳ ቢሆን ይደረግልሻል አላት።
3 ፤ ንግሥቲቱም አስቴር መልሳ። ንጉሥ ሆይ፥ በአንተ ዘንድ ሞገስ አግኝቼ እንደ ሆነ፥ ንጉሡንም ደስ ቢያሰኘው፥ ሕይወቴ በልመናዬ ሕዝቤም በመሻቴ ይሰጠኝ፤
4 ፤ እኔና ሕዝቤ ለመጥፋትና ለመገደል ለመደምሰስም ተሸጠናልና። ባርያዎች ልንሆን ተሸጠን እንደ ሆነ ዝም ባልሁ ነበር፤ የሆነ ሆኖ ጠላቱ የንጉሡን ጉዳት ለማቅናት ባልቻለም ነበር አለች።
5 ፤ ንጉሡም አርጤክስስ ንግሥቲቱን አስቴርን። ይህን ያደርግ ዘንድ በልቡ የደፈረ ማን ነው? እርሱስ ወዴት ነው? ብሎ ተናገራት።
6 ፤ አስቴርም። ያ ጠላትና ባለጋራ ሰው ክፉው ሐማ ነው አለች። ሐማም በንጉሡና በንግሥቲቱ ፊት ደነገጠ።
7 ፤ ንጉሡም ተቈጥቶ የወይን ጠጅ ከመጠጣቱ ተነሣ፥ ወደ ንጉሡም ቤት አታክልት ውስጥ ሄደ። ሐማም ከንጉሡ ዘንድ ክፉ ነገር እንደ ታሰበበት አይቶአልና ከንግሥቲቱ ከአስቴር ሕይወቱን ይለምን ዘንድ ቆመ።
8 ፤ ንጉሡም ከቤቱ አታክልት ወደ ወይን ጠጁ ግብዣ ስፍራ ተመለሰ፤ ሐማም አስቴር ባለችበት አልጋ ላይ ወድቆ ነበር። ንጉሡም። ደግሞ በቤቴ በእኔ ፊት ንግሥቲቱን ይጋፋታልን? አለ። ይህም ቃል ከንጉሡ አፍ በወጣ ጊዜ የሐማን ፊት ሸፈኑት።
9 ፤ በንጉሡም ፊት ካሉት ጃንደረቦች አንዱ ሐርቦና። እነሆ ሐማ ለንጉሡ በጎ ለተናገረው ለመርዶክዮስ ያሠራው ርዝመቱ አምሳ ክንድ የሆነው ግንድ በሐማ ቤት ተተክሎአል አለ። ንጉሡም። በእርሱ ላይ ስቀሉት አለ።
10 ፤ ሐማንም ለመርዶክዮስ ባዘጋጀው ግንድ ላይ ሰቀሉት፤ በዚያም ጊዜ የንጉሡ ቍጣ በረደ።