መጽሐፈ አስቴር።
ምዕራፍ 6
በዚያም ሌሊት እንቅልፍ ከንጉሡ ሸሸ፤ የዘመኑንም ታሪክ መጽሐፍ ያመጡ ዘንድ አዘዘ፥ በንጉሡም ፊት ተነበበ።
2 ፤ ደጁንም ከሚጠብቁት ከንጉሡ ጃንደረቦች ሁለቱ ገበታና ታራ እጃቸውን በንጉሡ በአርጤክስስ ላይ ያነሡ ዘንድ እንደ ፈለጉ፥ መርዶክዮስ እንደ ነገረው ተጽፎ ተገኘ።
3 ፤ ንጉሡም። ስለዚህ ነገር ለመርዶክዮስ ምን ክብርና በጎነት ተደረገለት? አለ። ንጉሡንም የሚያገለግሉ ብላቴኖች። ምንም አልተደረገለትም አሉት።
4 ፤ ንጉሡም። በአዳራሹ ማን አለ? አለ። ሐማም ባዘጋጀው ግንድ ላይ መርዶክዮስን ለማሰቀል ለንጉሡ ይናገር ዘንድ ወደ ንጉሡ ቤት ወደ ውጭው አዳራሽ ገብቶ ነበር።
5 ፤ የንጉሡም ብላቴኖች። እነሆ ሐማ በአዳራሹ ቆሞአል አሉት። ንጉሡም። ይግባ አለ።
6 ፤ ሐማም ገባ፤ ንጉሡም። ንጉሡ ሊያከብረው ለሚወድደው ሰው ምን ይደረግለታል? አለው። ሐማም በልቡ። ንጉሡ ከእኔ ይልቅ ማንን ያከብር ዘንድ ይወድዳል? አለ።
7 ፤ ሐማም ንጉሡን እንዲህ አለው። ንጉሡ ያከብረው ዘንድ ለሚወድደው ሰው እንዲህ ይደረግ፤
8 ፤ ንጉሡ የለበሰው የክብር ልብስ፥ ንጉሡም የተቀመጠበት ፈረስ ይምጣለት፥ የንጉሡም ዘውድ በራሱ ላይ ይደረግ፤
9 ፤ ልብሱንና ፈረሱንም ከንጉሡ አዛውንት በዋነኛው እጅ ያስረክቡት፤ ንጉሡም ያከብረው ዘንድ የሚወድደውን ሰው ያልብሱት፤ በፈረሱም ላይ አስቀምጠውት በከተማይቱ አደባባይ ያሳልፉት፤ በፊቱም። ንጉሡ ያከብረው ዘንድ ለሚወድደው ሰው እንዲህ ይደረግለታል ተብሎ አዋጅ ይነገር።
10 ፤ ንጉሡም ሐማን። ፍጠን፥ እንደ ተናገርኸውም ልብሱንና ፈረሱን ውሰድ፤ በንጉሡም በር ለሚቀመጠው አይሁዳዊ ለመርዶክዮስ እንዲሁ አድርግለት፤ ከተናገርኸውም ሁሉ ምንም አይቅር አለው።
11 ፤ ሐማም ልብሱንና ፈረሱን ወሰደ፥ መርዶክዮስንም አለበሰው፥ በፈረሱም ላይ አስቀመጠው፥ በከተማይቱም አደባባይ በፊቱ አሳለፈው። በፊቱም። ንጉሡ ያከብረው ዘንድ ለሚወድደው ሰው እንዲህ ይደረግለታል ብሎ አዋጅ ነገረ።
12 ፤ መርዶክዮስም ወደ ንጉሡ በር ተመለሰ። ሐማ ግን አዝኖና ራሱን ተከናንቦ ቸኵሎ ወደ ቤቱ ሄደ።
13 ፤ ሐማም ለሚስቱ ለዞሳራና ለወዳጆቹ ሁሉ ያገኘውን ሁሉ አጫወታቸው። ጥበበኞቹና ሚስቱ ዞሳራም። በፊቱ መውደቅ የጀመርህለት መርዶክዮስ ከአይሁድ ወገን የሆነ እንደ ሆነ በፊቱ ፈጽሞ ትወድቃለህ እንጂ አታሸንፈውም አሉት።
14 ፤ እነርሱም ሲናገሩት ሳሉ እነሆ የንጉሡ ጃንደረቦች መጡ፥ አስቴርም ወዳዘጋጀችው ግብዣ ይመጣ ዘንድ ሐማን አስቸኰሉት።