ትንቢተ ሚልክያ

1 2 3 4


ምዕራፍ 3

እነሆ፥ መልእክተኛዬን እልካለሁ፥ መንገድንም በፊቴ ያስተካክላል፤ እናንተም የምትፈልጉት ጌታ በድንገት ወደ መቅደሱ ይመጣል፤ የምትወዱትም የቃል ኪዳን መልእክተኛ፥ እነሆ፥ ይመጣል፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር።
2 ፤ ነገር ግን እርሱ እንደ አንጥረኛ እሳትና እንደ አጣቢ ሳሙና ነውና የሚመጣበትን ቀን መታገሥ የሚችል ማን ነው? እርሱስ በተገለጠ ጊዜ የሚቆም ማን ነው?
3 ፤ እርሱም ብርን እንደሚያነጥርና እንደሚያጠራ ሰው ይቀመጣል፥ የሌዊንም ልጆች ያጠራል፥ እንደ ወርቅና እንደ ብርም ያነጥራቸዋል፤ እነርሱም ለእግዚአብሔር በጽድቅ ቍርባንን የሚያቀርቡ ይሆናሉ።
4 ፤ እግዚአብሔርም እንደ ዱሮው ዘመንና እንደ ቀደሙት ዓመታት በይሁዳና በኢየሩሳሌም ቍርባን ደስ ይለዋል።
5 ፤ ለፍርድ ወደ እናንተ እቀርባለሁ፤ በመተተኞችና በአመንዝሮች፥ በሐሰትም በሚምሉ፥ የምንደኛውን ደመወዝ በሚከለክሉ፥ መበለቲቱንና ድሀ አደጉን በሚያስጨንቁ፥ የመጻተኛውንም ፍርድ በሚያጣምሙ፥ እኔንም በማይፈሩ ላይ ፈጣን ምስክር እሆንባቸዋለሁ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር።
6 ፤ እኔ እግዚአብሔር አልለወጥም፤ እናንተ የያዕቆብ ልጆች ሆይ፥ ስለዚህ የጠፋችሁ አይደላችሁም።
7 ፤ ከአባቶቻችሁ ዘመን ጀምር ከሥርዓቴ ፈቀቅ ብላችኋል፥ እርስዋንም አልጠበቃችሁም። ወደ እኔ ተመለሱ፥ እኔም ወደ እናንተ እመለሳለሁ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር። እናንተ ግን። የምንመለሰው በምንድር ነው? ብላችኋል።
8 ፤ ሰው እግዚአብሔርን ይሰርቃልን? እናንተ ግን እኔን ሰርቃችኋል። እናንተም። የሰረቅንህ በምንድር ነው? ብላችኋል። በአሥራትና በበኵራት ነው።
9 ፤ እናንተ፥ ይህ ሕዝብ ሁሉ፥ እኔን ሰርቃችኋልና በእርግማን ርጉሞች ናችሁ።
10 ፤ በቤቴ ውስጥ መብል እንዲሆን አሥራቱን ሁሉ ወደ ጎተራ አግቡ፤ የሰማይንም መስኮት ባልከፍትላችሁ፥ በረከትንም አትረፍርፌ ባላፈስስላችሁ በዚህ ፈትኑኝ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር።
11 ፤ ስለ እናንተ ነቀዙን እገሥጻለሁ፥ የምድራችሁንም ፍሬ አያጠፋም፤ በእርሻችሁም ያለው ወይን ፍሬውን አያረግፍም፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር።
12 ፤ የተድላ ምድር ትሆናላችሁና አሕዛብ ሁሉ ብፁዓን ብለው ይጠሩአችኋል፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር።
13 ፤ ቃላችሁ በእኔ ላይ ድፍረት ሆኖአል፥ ይላል እግዚአብሔር። እናንተ ግን። በአንተ ላይ ደፍረን የተናገርነው በምንድር ነው? ብላችኋል።
14 ፤ እናንተም። እግዚአብሔርን ማገልገል ከንቱ ነው፤ ትእዛዙንስ በመጠበቅ፥ በሠራዊት ጌታ በእግዚአብሔር ፊት ኀዘንተኞች ሆነን በመሄድ ምን ይረባናል?
15 ፤ አሁንም የሚታበዩትን ሰዎች ብፁዓን ብለን እንጠራቸዋለን፤ ክፉንም የሚሠሩ ጸንተዋል እግዚአብሔርንም ይፈታተናሉ፥ ያመልጣሉም ብላችኋል።
16 ፤ የዚያን ጊዜ እግዚአብሔርን የሚፈሩ እርስ በእርሳቸው ተነጋገሩ፤ እግዚአብሔርም አደመጠ፥ ሰማም፥ እግዚአብሔርንም ለሚፈሩ ስሙንም ለሚያስቡ የመታሰቢያ መጽሐፍ በፊቱ ተጻፈ።
17 ፤ እኔ በምሠራበት ቀን እነርሱ የእኔ ገንዘብ ይሆናሉ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፤ ሰውም የሚያገለግለውን ልጁን እንደሚምር፥ እንዲሁ እምራቸዋለሁ።
18 ፤ ተመልሳችሁም በጻድቁና በኃጢአተኛው መካከል፥ ለእግዚአብሔር በሚገዛውና በማይገዛው መካከል ትለያላችሁ።