ትንቢተ ሚልክያ

1 2 3 4


ምዕራፍ 2

አሁንም እናንተ ካህናት ሆይ፥ ይህ ትእዛዝ ለእናንተ ነው።
2 ፤ ለስሜ ክብር ትሰጡ ዘንድ ባትሰሙ፥ በልባችሁም ባታደርጉት፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፥ እርግማን እሰድድባችኋለሁ፥ በረከታችሁንም እረግማታለሁ፤ አሁንም በልባችሁ አላደረጋችሁትምና እኔ ረግሜአታለሁ።
3 ፤ እነሆ፥ ክንዳችሁን እገሥጻለሁ፥ የመሥዋዕታችሁንም ፋንድያ በፊታችሁ ላይ እበትናለሁ፤ ከእርሱም ጋር በአንድነት ትወሰዳላችሁ።
4 ፤ ቃል ኪዳኔ ከሌዊ ጋር ይሆን ዘንድ ይህን ትእዛዝ እንደ ሰደድሁላችሁ ታውቃላችሁ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር።
5 ፤ ቃል ኪዳኔ ከእርሱ ጋር የሕይወትና የሰላም ቃል ኪዳን ነበረ፤ ይፈራ ዘንድም እነርሱን ሰጠሁት፤ እርሱም ፈራኝ፥ ከስሜም የተነሣ ደነገጠ።
6 ፤ የእውነት ሕግ በአፉ ውስጥ ነበረች፥ በከንፈሩም ውስጥ በደል አልተገኘበትም፤ ከእኔም ጋር በሰላምና በቅንነት ሄደ፥ ብዙ ሰዎችንም ከኃጢአት መለሰ።
7 ፤ ካህኑ የሠራዊት ጌታ የእግዚአብሔር መልእክተኛ ነውና ከንፈሮቹ እውቀትን ይጠብቁ ዘንድ ይገባቸዋል፥ ሰዎችም ሕግን ከአፉ ይፈልጉ ዘንድ ይገባቸዋል።
8 ፤ እናንተ ግን ከመንገዱ ፈቀቅ ብላችኋል፤ በሕግም ብዙ ሰዎችን አሰናክላችኋል፤ የሌዊንም ቃል ኪዳን አስነውራችኋል፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር።
9 ፤ ስለዚህ መንገዴን እንዳልጠበቃችሁ፥ በሕግም ለሰው ፊት እንዳዳላችሁ መጠን፥ እኔ ደግሞ በሕዝብ ሁሉ ፊት የተናቃችሁና የተዋረዳችሁ አድርጌአችኋለሁ።
10 ፤ ለሁላችን አንድ አባት ያለን አይደለምን? አንድ አምላክስ የፈጠረን አይደለምን? የአባቶቻችንን ቃል ኪዳን ለማስነቀፍ እኛ እያንዳንዳችን ወንድማችንን ስለ ምን አታለልን?
11 ፤ እግዚአብሔር የወደደውን መቅደስ ይሁዳ አርክሶአልና፥ የእንግዳውንም አምላክ ልጅ ሚስት አድርጎ አግብቶአልና ይሁዳ አታልሎአል፥ በእስራኤልና በኢየሩሳሌም ውስጥ ርኵሰት ተሠርቶአል።
12 ፤ ይህን ከሚያደርግ ሰው፥ እግዚአብሔር የሚጠራውንና የሚመልሰውን ለሠራዊትም ጌታ ለእግዚአብሔር ቍርባን የሚያቀርበውን ከያዕቆብ ድንኳን ያጠፋል።
13 ፤ ይህንም ደግሞ አድርጋችኋል፤ እግዚአብሔር ቍርባኑን ዳግመኛ እንዳይመለከት፥ ከእጃችሁም በደስታ እንዳይቀበለው መሠዊያውን በእንባና በልቅሶ በኀዘንም ትከድናላችሁ።
14 ፤ እናንተም። ስለ ምንድር ነው? ብላችኋል። ሚስትህ ባልንጀራህና የቃል ኪዳንህ ሚስት ሆና ሳለች እርስዋን አታልለሃታልና እግዚአብሔር በአንተና በልጅነት ሚስትህ መካከል ምስክር ስለ ሆነ ነው።
15 ፤ እግዚአብሔር የሕይወትን መንፈስ አንድ አድርጎ ጠብቆልን የለምን? እርሱም የሚፈልገው ምንድር ነው? ዘር አይደለምን? ስለዚህ መንፈሳችሁን ጠብቁ፥ ማንም የልጅነት ሚስቱን አያታልል።
16 ፤ መፋታትን እጠላለሁ፥ ይላል የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር፥ ልብሱንም በግፍ ሥራ የሚከድነውን ሰው እጠላለሁ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፤ ስለዚህ እንዳታታልሉ መንፈሳችሁን ጠብቁ።
17 ፤ እግዚአብሔርን በቃላችሁ አታክታችኋል። እናንተም። ያታከትነው በምንድር ነው? ብላችኋል። ክፉን የሚያደርግ ሁሉ በእግዚአብሔር ዘንድ መልካም ነው፥ እርሱም በእነርሱ ደስ ይለዋል፤ ወይስ። የፍርድ አምላክ ወዴት አለ? በማለታችሁ ነው።