ትንቢተ ዕንባቆም

1 2 3


ምዕራፍ 3

የነቢዩ የዕንባቆም ጸሎት በመዝሙር።
2 ፤ አቤቱ፥ ዝናህን ሰምቼ ፈራሁ፤ አቤቱ፥ በዓመታት መካከል ሥራህን ፈጽም፤ በዓመታት መካከል ትታወቅ፤ በመዓት ጊዜ ምሕረትን አስብ።
3 ፤ እግዚአብሔር ከቴማን፥ ቅዱሱም ከፋራን ተራራ ይመጣል። ክብሩ ሰማያትን ከድኖአል፥ ምስጋናውም ምድርን ሞልቶአል።
4 ፤ ፀዳሉም እንደ ብርሃን ነው፤ ጨረር ከእጁ ወጥቶአል፤ ኃይሉም በዚያ ተሰውሮአል።
5 ፤ ቸነፈር በፊቱ ይሄዳል፥ የእሳትም ነበልባል ከእግሩ ይወጣል።
6 ፤ ቆመ፥ ምድርንም አወካት፤ ተመለከተ፥ አሕዛብንም አናወጠ፤ የዘላለምም ተራሮች ተቀጠቀጡ፥ የዘላለምም ኮረብቶች ቀለጡ፤ መንገዱ ከዘላለም ነው።
7 ፤ የኢትዮጵያ ድንኳኖች ሲጨነቁ አየሁ፤ የምድያም አገር መጋረጃዎች ተንቀጠቀጡ።
8 ፤ በውኑ እግዚአብሔር በወንዞች ላይ ተቈጥቶአልን? ቍጣህ በወንዞች ላይ፥ መዓትህም በባሕር ላይ ነውን? በፈረሶችህና በማዳንህ ሰረገሎች ላይ ተቀምጠሃልና።
9 ፤ በቃልህ እንደ ማልህ መቅሠፍትህን አወጣህ፤ ቀስትህንም ገተርህ፤ ምድርን ሰንጥቀህ ፈሳሾችን አወጣህ።
10 ፤ ተራሮች አንተን አይተው ተጨነቁ፤ የውኃ ሞገድ አልፎአል፤ ቀላዩም ድምፁን ሰጥቶአል፥ እጁንም ወደ ላይ አንሥቶአል።
11 ፤ ፍላጾችህ ከወጡበት ብርሃን የተነሣ፥ ከሚንቦገቦገውም ከጦርህ ፀዳል የተነሣ፥ ፀሐይና ጨረቃ በመኖሪያቸው ቆሙ።
12 ፤ በምድር ላይ በመዓት ተራመድህ፤ አሕዛብን በቍጣ አሄድሃቸው።
13 ፤ ሕዝብህን ለመታደግ፥ የቀባኸውንም ለማዳን ወጣህ፤ የኃጢአተኛውን ቤት ራስ ቀጠቀጥህ፤ መሠረቱን እስከ አንገቱ ድረስ ገለጥህ።
14 ፤ የአለቆችን ራስ በገዛ በትራቸው ወጋህ፤ እኔን ይበትኑ ዘንድ እንደ ዐውሎ ነፋስ መጡ፤ ችግረኛውን በስውር ለመዋጥ ደስታቸው ነው።
15 ፤ ፈረሶችህን በባሕር፥ በብዙ ውኆችም ላይ አስረገጥህ።
16 ፤ እኔ ሰምቻለሁ፥ ልቤም ደነገጠብኝ፤ ከድምፁ የተነሣ ከንፈሮቼ ተንቀጠቀጡ፤ መንቀጥቀጥ ወደ አጥንቶቼ ውስጥ ገባ፤ በስፍራዬ ሆኜ ተናወጥሁ፤ በሚያስጨንቁን ሕዝብ ላይ እስኪመጣ ድረስ የመከራን ቀን ዝም ብዬ እጠብቃለሁ።
17 ፤ ምንም እንኳ በለስም ባታፈራ፥ በወይንም ሐረግ ፍሬ ባይገኝ፥ የወይራ ሥራ ቢጐድል፥ እርሾችም መብልን ባይሰጡ፥ በጎች ከበረቱ ቢጠፉ፥ ላሞችም በጋጡ ውስጥ ባይገኙ፥
18 ፤ እኔ ግን በእግዚአብሔር ደስ ይለኛል፤ በመድኃኒቴ አምላክ ሐሤት አደርጋለሁ።
19 ፤ ጌታ እግዚአብሔር ኃይሌ ነው፤ እግሮቼን እንደ ዋላ እግሮች ያደርጋል፤ በከፍታዎችም ላይ ያስሄደኛል።