ትንቢተ ዕንባቆም

1 2 3


ምዕራፍ 2

በመጠበቂያዬ ላይ እቆማለሁ፥ በአምባ ላይም እወጣለሁ፤ የሚናገረኝንም፥ ስለ ክርክሬም የምመልሰውን አውቅ ዘንድ እመለከታለሁ።
2 ፤ እግዚአብሔርም መለሰልኝ እንዲህም አለ። አንባቢው ይፈጥን ዘንድ ራእዩን ጻፍ፥ በጽላትም ላይ ግለጠው።
3 ፤ ራእዩ ገና እስከ ተወሰነው ጊዜ ነው፥ ወደ ፍጻሜውም ይቸኵላል፥ እርሱም አይዋሽም፤ ቢዘገይም በእርግጥ ይመጣልና ታገሠው፤ እርሱ አይዘገይም።
4 ፤ እነሆ፥ ነፍሱ ኰርታለች፥ በውስጡም ቅን አይደለችም፤ ጻድቅ ግን በእምነቱ በሕይወት ይኖራል።
5 ፤ እርሱ አታላይና ኵሩ ሰው ነው፤ በስፍራው ዐርፎ አይቀመጥም፤ ስስቱን እንደ ሲኦል ያሰፋል፥ እርሱም እንደ ሞት አይጠግብም፤ አሕዛብንም ሁሉ ወደ እርሱ ይሰበስባል፥ ወገኖቹንም ሁሉ ወደ እርሱ ያከማቻል።
6 ፤ እነዚህ ሁሉ። ለእርሱ ያልሆነውን ወደ እርሱ ለሚሰበስብ መያዣውንም ለራሱ የሚያበዛ ወዮለት! እስከ መቼ ነው? እያሉ ምሳሌ አይመስሉበትምን?
7 ፤ ተረትም አይተርቱበትምን? የሚነክሱህ ድንገት አይነሡብህምን? የሚያስጨንቁህም ይነቃሉ፤ ለእነርሱም ብዝበዛ ትሆናለህ።
8 ፤ የሰውን ደም ስላፈሰስህ፥ በምድሪቱና በከተማይቱም በእርስዋም በሚኖሩ ሁሉ ላይ ስላደረግኸው ግፍ፥ አንተ ብዙዎችን አሕዛብን በዝብዘሃልና ከአሕዛብ የቀሩት ሁሉ ይበዘብዙሃል።
9 ፤ ከክፉ እንዲድን ጐጆውን በከፍታ ላይ ያደርግ ዘንድ ለቤቱ ክፉ ትርፍን ለሚሰበስብ ወዮለት!
10 ፤ ብዙ አሕዛብን አጥፍተሃልና ለቤትህ እፍረትን መክረሃል፥ በነፍስህም ላይ ኃጢአትን አድርገሃል።
11 ፤ ድንጋይም ከግንብ ውስጥ ይጮኻል፥ እንጨትም ከውቅር ውስጥ ይመልስለታል።
12 ፤ ከተማን በደም ለሚሠራ፥ ከተማንም በኃጢአት ለሚመሠርት ወዮለት!
13 ፤ እነሆ፥ አሕዛብ ስለ እሳት እንዲሠሩ፥ ወገኖችም ስለ ከንቱነት እንዲደክሙ ከሠራዊት ጌታ ከእግዚአብሔር ዘንድ የሆነ አይደለምን?
14 ፤ ውኃ ባሕርን እንደሚከድን ምድር የእግዚአብሔርን ክብር በማወቅ ትሞላለችና።
15 ፤ ኀፍረተ ሥጋውን ለማየት ባልንጀራውን ለሚያጠጣ፥ ክፉንም ለሚጨምርበት፥ ለሚያሰክረውም ወዮለት!
16 ፤ በክብር ፋንታ እፍረት ሞልቶብሃል፤ አንተ ደግሞ ጠጥተህ ተንገድገድ፤ የእግዚአብሔር የቀኙ ጽዋ ይመለስብሃል፥ እፍረትም በክብርህ ላይ ይሆናል።
17 ፤ የሰውንም ደም ስላፈሰስህ፥ በምድሪቱና በከተማይቱም በእርስዋም በሚኖሩ ሁሉ ላይ ስላደረግኸው ግፍ፥ በሊባኖስ ላይ የሠራኸው ግፍ ይከድንሃል፤ የአራዊትም አደጋ ያስፈራራሃል።
18 ፤ የተቀረጸውን ምስል ሠሪው የቀረጸው ለምን ጥቅም ነው? ዲዳንም ጣዖት ይሠራ ዘንድ ሠሪው የታመነበቱ፥ ሐሰትን የሚያስተምር ቀልጦ የተሠራ ምን ይጠቅማል?
19 ፤ እንጨቱን። ንቃ፥ ዲዳውንም ድንጋይ። ተነሣ ለሚለው ወዮለት! በውኑ ይህ ያስተምራልን? እነሆ፥ በወርቅና በብር ተለብጦአል፥ ምንም እስትንፋስ የለበትም።
20 ፤ እግዚአብሔር ግን በተቀደሰ መቅደሱ አለ፤ ምድርም ሁሉ በፊቱ ዝም ትበል።