ትንቢተ ዳንኤል

1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12


ምዕራፍ 8

በመጀመሪያ ከተገለጠልኝ ራእይ በኋላ፥ ንጉሡ ብልጣሶር በነገሠ በሦስተኛው ዓመት፥ ለእኔ ለዳንኤል ራእይ ተገለጠልኝ።
2 ፤ በራእዩም አየሁ፤ ባየሁም ጊዜ በኤላም አውራጃ ባለው በሱሳ ግንብ ነበርሁ፤ በራእዩም አየሁ በኡባል ወንዝም አጠገብ ነበርሁ።
3 ፤ ዓይኔን አንሥቼ አየሁ፤ እነሆም፥ ሁለት ቀንዶች የነበሩት አንድ አውራ በግ በወንዙ ፊት ቆሞ ነበር፥ ሁለቱም ቀንዶቹ ከፍ ከፍ ይሉ ነበር፤ አንዱ ግን ከሁለተኛው ከፍ ያለ ነበረ፥ ታላቁም ወደ ኋላው ወጥቶ ነበር።
4 ፤ አውራውም በግ ወደ ምዕራብ ወደ ሰሜንም ወደ ደቡብም በቀንዱ ሲጐሽም አየሁ፤ አራዊትም ሁሉ ይቋቋሙት ዘንድ አልቻሉም፥ ከእጁም የሚያድን አልነበረም፤ እንደ ፈቃዱም አደረገ፥ ራሱንም ታላቅ አደረገ።
5 ፤ እኔም ስመለከት፥ እነሆ፥ ከምዕራብ ወገን አንድ አውራ ፍየል በምድር ሁሉ ፊት ላይ ወጣ፥ ምድርንም አልነካም፤ ለፍየሉም በዓይኖቹ መካከል አንድ ታላቅ ቀንድ ነበረው።
6 ፤ ሁለትም ቀንድ ወዳለው በወንዝም ፊት ቆሞ ወዳየሁት አውራ በግ መጣ፥ በኃይሉም ቍጣ ፈጥኖ ወደ እርሱ ሮጠ።
7 ፤ ወደ አውራውም በግ ሲቀርብ አየሁት፤ እርሱም ተመረረበት፥ አውራውንም በግ መታ፥ ሁለቱንም ቀንዶች ሰበረ፤ አውራውም በግ ሊቋቋመው ኃይል አልነበረውም፥ እርሱም በምድር ላይ ጥሎ ረገጠው፤ አውራውንም በግ ከእጁ ያድነው ዘንድ የሚችል አልነበረም።
8 ፤ አውራውም ፍየል ራሱን እጅግ ታላቅ አደረገ፤ በበረታም ጊዜ ታላቁ ቀንዱ ተሰበረ፥ ወደ አራቱም የሰማይ ነፋሳት የሚመለከቱ አራት ቀንዶች ከበታቹ ወጡ።
9 ፤ ከእነርሱም ከአንደኛው አንድ ታናሽ ቀንድ ወጣ፥ ወደ ደቡብም ወደ ምሥራቅም ወደ መልካሚቱም ምድር እጅግ ከፍ አለ።
10 ፤ እስከ ሰማይም ሠራዊት ድረስ ከፍ አለ፤ ከሠራዊትና ከከዋክብትም አያሌዎችን ወደ ምድር ጣለ፥ ረገጣቸውም።
11 ፤ እስከ ሠራዊትም አለቃ ድረስ ራሱን ታላቅ አደረገ፤ ከእርሱም የተነሣ የዘወትሩ መሥዋዕት ተሻረ፥ የመቅደሱም ስፍራ ፈረሰ።
12 ፤ ሠራዊቱም ከኃጢአት የተነሣ ከዘወትሩ መሥዋዕት ጋር ተሰጠው፤ እርሱም እውነትን ወደ ምድሩ ጣለ፥ አደረገም ተከናወነም።
13 ፤ ከቅዱሳኑም አንዱ ሲናገር ሰማሁ፤ ለተናገረው ለቅዱሱም ሁለተኛው ቅዱስ። ስለ ዘወትሩ መሥዋዕት፥ መቅደሱና ሠራዊቱም ይረገጡ ዘንድ ስለሚሰጥና ስለሚያጠፋ ኃጢአት የሆነው ራእይ እስከ መቼ ይሆናል? አለው።
14 ፤ እርሱም። እስከ ሁለት ሺህ ሦስት መቶ ማታና ጥዋት ድረስ ነው፤ ከዚያም በኋላ መቅደሱ ይነጻል አለኝ።
15 ፤ እኔም ዳንኤል ራእዩን ባየሁ ጊዜ ማስተዋሉን ፈለግሁ፤ እነሆም፥ የሰው ምስያ በፊቴ ቆሞ ነበር።
16 ፤ በኡባልም ወንዝ መካከል። ገብርኤል ሆይ፥ ራእዩን ለዚህ ሰው አስታውቀው ብሎ የሚጮኸውን የሰውን ድምፅ ሰማሁ።
17 ፤ እኔም ወደ ቆምሁበት ቀረበ፤ በመጣም ጊዜ ፈርቼ በግምባሬ ተደፋሁ፤ እርሱም። የሰው ልጅ ሆይ፥ ራእዩ ለፍጻሜ ዘመን እንደ ሆነ አስተውል አለኝ።
18 ፤ ሲናገረኝም ደንግጬ በምድር ላይ በግምባሬ ተደፋሁ፤ እርሱም ዳሰሰኝ ቀጥ አድርጎም አቆመኝ።
19 ፤ እንዲህም አለኝ። እነሆ፥ በመቅሠፍቱ በመጨረሻ ዘመን የሚሆነውን አስታውቅሃለሁ፤ ይህ ለተወሰነው ለፍጻሜ ዘመን ነውና።
20 ፤ ባየኸው በአውራው በግ ላይ የነበሩ ሁለቱ ቀንዶች እነርሱ የሜዶንና የፋርስ ነገሥታት ናቸው።
21 ፤ አውራውም ፍየል የግሪክ ንጉሥ ነው፤ በዓይኖቹም መካከል ያለው ታላቁ ቀንድ መጀመሪያው ንጉሥ ነው።
22 ፤ እርሱም በተሰበረ ጊዜ በእርሱ ፋንታ አራቱ እንደ ተነሡ፥ እንዲሁ ከወገኑ አራት መንግሥታት ይነሣሉ፥ ነገር ግን በኃይል አይተካከሉትም።
23 ፤ በመንግሥታቸውም መጨረሻ፥ ኃጢአታቸው በተሞላች ጊዜ፥ እንቈቅልሽን የሚያስተውል ፊተ ጨካኝ ንጉሥ ይነሣል።
24 ፤ ኃይሉም ይበረታል፥ ነገር ግን በራሱ ኃይል አይደለም፤ በድንቅም ያጠፋል፥ ያደርግማል፥ ይከናወንማል፤ ኃያላንንና የቅዱሳንን ሕዝብ ያጠፋል።
25 ፤ በመታለሉ ተንኰልን በእጁ ያከናውናል፤ በልቡም ይታበያል፥ ታምነውም የሚኖሩትን ብዙዎችን ያጠፋል፤ በአለቆቹም አለቃ ላይ ይቋቋማል፤ ያለ እጅም ይሰበራል።
26 ፤ የተነገረውም የማታውና የጥዋቱ ራእይ እውነተኛ ነው፤ ነገር ግን ከብዙ ዘመን በኋላ ስለሚሆን ራእዩን ዝጋ።
27 ፤ እኔም ዳንኤል ተኛሁ፥ አያሌም ቀን ታመምሁ፤ ከዚያም በኋላ ተነሥቼ የንጉሡን ሥራ እሠራ ነበር፤ ስለ ራእዩም አደንቅ ነበር፥ የሚያስተውለው ግን አልነበረም።