ትንቢተ ዳንኤል

1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12


ምዕራፍ 11

እኔም በሜዶናዊ በዳርዮስ መጀመሪያ ዓመት አጸናውና አበረታው ዘንድ ቆሜ ነበር።
2 ፤ አሁንም እውነትን አሳይሃለሁ። እነሆ፥ ሦስት ነገሥታት ደግሞ በፋርስ ይነሣሉ፤ አራተኛውም ከሁሉ ይልቅ እጅግ ባለጠጋ ይሆናል፤ በባለጠግነቱም በበረታ ጊዜ በግሪክ መንግሥት ላይ ሁሉን ያስነሣል።
3 ፤ ኃያልም ንጉሥ ይነሣል፥ በትልቅ አገዛዝም ይገዛል፥ እንደ ፈቃዱም ያደርጋል።
4 ፤ እርሱም በተነሣ ጊዜ መንግሥቱ ይሰበራል፤ እስከ አራቱ የሰማይ ነፋሳት ይከፋፈላል። ለዘሩ ግን አይከፋፈልም፥ እንደ ገዛበትም አገዛዝ አይሆንም፤ መንግሥቱ ይነቀላልና፤ ከእነዚህም ለሌሎች ይሆናልና።
5 ፤ የደቡብም ንጉሥ ከአለቆቹም አንዱ ይበረታሉ፤ እርሱም ይበረታበታል ይሠለጥንማል፤ ግዛቱም ታላቅ ግዛት ይሆናል።
6 ፤ ከዘመናትም በኋላ ይጋጠማሉ፤ የደቡብም ንጉሥ ሴት ልጅ ቃል ኪዳን ለማድረግ ወደ ሰሜን ንጉሥ ትመጣለች፤ የክንድዋ ኃይል ግን አይጸናም፥ እርሱና ክንዱም አይጸናም፤ እርስዋና እርስዋን ያመጡ የወለዳትም በዚያም ዘመን ያጸናት አልፈው ይሰጣሉ።
7 ፤ ነገር ግን ከሥርዋ ቍጥቋጥ አንዱ በስፍራው ይነሣል፤ ወደ ሠራዊቱም ይመጣል፥ ወደ ሰሜንም ንጉሥ አምባ ይገባል፥ በላያቸውም ያደርጋል፥ ያሸንፍማል።
8 ፤ አማልክቶቻቸውንና ቀልጠው የተሠሩትን ምስሎቻቸውን ከብርና ከወርቅም የተሠሩትን የከበሩትን ዕቃዎች ወደ ግብጽ ይማርካል፤ እስከ ጥቂትም ዓመት ድረስ ከሰሜን ንጉሥ ጋር ሳይዋጋ ይቀመጣል።
9 ፤ ይህም ወደ ደቡብ ንጉሥ መንግሥት ይገባል፥ ነገር ግን ወደ ገዛ ምድሩ ይመለሳል።
10 ፤ ልጆቹም ይዋጋሉ፤ ብዙ ሠራዊትንና ሕዝብን ይሰበስባል፤ እርሱም ይመጣል፥ ይጐርፍማል፥ ያልፍማል፤ ተመልሶም እስከ አምባው ድረስ ይዋጋል።
11 ፤ የደቡብም ንጉሥ ይቈጣል ወጥቶም ከሰሜን ንጉሥ ጋር ይዋጋል፤ ብዙ ሕዝብንም ለሰልፍ ያቆማል፥ ሕዝቡም አልፎ በእጁ ይሰጣል።
12 ፤ ሕዝቡም በተወሰደ ጊዜ ልቡ ይታበያል፤ አእላፋትንም ይጥላል፥ ነገር ግን አያሸንፍም።
13 ፤ የሰሜንም ንጉሥ ይመለሳል፥ ከቀደመውም የበለጠ ብዙ ሕዝብ ለሰልፍ ያቆማል፤ በዘመናትና በዓመታትም ፍጻሜ ከታላቅ ሠራዊትና ከብዙ ሀብት ጋር ይመጣል።
14 ፤ በዚያም ዘመን ብዙ ሰዎች በደቡብ ንጉሥ ላይ ይነሣሉ፤ ከሕዝብህም መካከል የዓመፅ ልጆች ራእዩን ያጸኑ ዘንድ ይነሣሉ፤ ነገር ግን ይወድቃሉ።
15 ፤ የሰሜንም ንጉሥ ይመጣል፥ አፈርንም ይደለድላል፥ የተመሸገችንም ከተማ ይወስዳል፤ የደቡብም ሠራዊት የተመረጡትም ሕዝቡ አይቆሙም፤ ለመቋቋምም ኃይል የላቸውም።
16 ፤ በእርሱም ላይ የሚመጣው ግን እንደ ፈቃዱ ያደርጋል፥ በፊቱም የሚቆም የለም፤ በመልካሚቱም ምድር ይቆማል፥ በእጁም ውስጥ ጥፋት ይሆናል።
17 ፤ ከመንግሥቱም ሁሉ ኃይል ጋር ይመጣ ዘንድ ፊቱን ያቀናል፥ ከእርሱም ጋር አንድነትን ያደርጋል፤ ያረክሳትም ዘንድ ሴትን ልጅ ይሰጠዋል፤ እርስዋም አትጸናም ለእርሱም አትሆንም።
18 ፤ ከዚህም በኋላ ፊቱን ወደ ደሴቶች ይመልሳል፥ ብዙዎችንም ይወስዳል፤ አንድ አለቃ ግን ስድቡን ይሽራል፥ ስድቡንም በራሱ ላይ ይመልሳል።
19 ፤ ፊቱንም ወደ ገዛ ምድሩ አምባዎች ይመልሳል፤ ተሰናክሎም ይወድቃል፥ አይገኝምም።
20 ፤ የዚያን ጊዜም በመንግሥቱ ክብር መካከል አስገባሪውን የሚያሳልፍ በስፍራው ይነሣል፤ ነገር ግን በቍጣው ሳይሆን በሰልፍም ሳይሆን በጥቂት ቀን ይሰበራል።
21 ፤ በእርሱም ስፍራ የተጠቃ ሰው ይነሣል የመንግሥቱንም ክብር አይሰጡትም፤ በቀስታ መጥቶ መንግሥቱን በማታለል ይገዛል።
22 ፤ የሚጐርፍም ሠራዊት ከፊቱ ይወሰዳል፥ እርሱና የቃል ኪዳኑ አለቃ ይሰበራሉ።
23 ፤ ከእርሱም ጋር ከተወዳጀ በኋላ በተንኰል ያደርጋል፤ ከጥቂትም ሕዝብ ጋር ወጥቶ ይበረታል።
24 ፤ በቀስታ ከአገር ሁሉ ወደ ለመለመችው ክፍል ይገባል፤ አባቶቹና የአባቶቹ አባቶች ያላደረጉትንም ያደርጋል፤ ብዝበዛውንና ምርኮውንም ሀብቱንም በመካከላቸው ይበትናል፤ በምሽጎችም ላይ እስከ ጊዜው ድረስ አሳቡን ይፈጥራል።
25 ፤ በታላቅም ሠራዊት ሆኖ ኃይሉንና ልቡን በደቡብ ንጉሥ ላይ ያስነሣል፤ የደቡብም ንጉሥ በታላቅና በብዙ ሠራዊት ሆኖ በሰልፍ ይዋጋል፤ ነገር ግን አሳብ በእርሱ ላይ ይፈጥራሉና አይጸናም።
26 ፤ መብሉንም የሚበሉ ሰዎች ይሰብሩታል፤ ሠራዊቱም ይጐርፋል፤ ብዙዎችም ተገድለው ይወድቃሉ።
27 ፤ እነዚህም ሁለት ነገሥታት ክፋትን ያደርጉ ዘንድ በልባቸው ያስባሉ፥ በአንድ ገበታም ተቀምጠው ሐሰት ይናገራሉ፤ ነገር ግን ፍጻሜው እስከ ተወሰነው ጊዜ ነውና አይከናወንላቸውም።
28 ፤ ከብዙም ሀብት ጋር ወደ ምድሩ ይመለሳል፥ ልቡም በተቀደሰ ቃል ኪዳን ላይ ይሆናል፤ ፈቃዱንም ያደርጋል፥ ወደ ገዛ ምድሩም ይመለሳል።
29 ፤ በተወሰነውም ጊዜ ይመለሳል ወደ ደቡብም ይመጣል፤ ነገር ግን ኋለኛው እንደ ፊተኛው አይሆንም።
30 ፤ የኪቲም መርከቦች ይመጡበታልና ስለዚህ አዝኖ ይመለሳል፥ በቅዱሱም ቃል ኪዳን ላይ ይቈጣል፥ ፈቃዱንም ያደርጋል፤ ተመልሶም ቅዱሱን ቃል ኪዳን የተዉትን ሰዎች ይመለከታል።
31 ፤ ከእርሱም ጋር ሠራዊቶች ይቆማሉ፥ መቅደሱንም ግንቡንም ያረክሳሉ፥ የዘወትሩንም መሥዋዕት ያስቀራሉ፥ የጥፋትንም ርኵሰት ያቆማሉ።
32 ፤ ቃል ኪዳኑን የሚበድሉትንም በማታለል ያስታል፤ ነገር ግን አምላካቸውን የሚያውቁ ሕዝብ ይበረታሉ፥ ያደርጋሉም።
33 ፤ በሕዝቡም መካከል ያሉ ጥበበኞች ብዙ ሰዎችን ያስተምራሉ፤ ነገር ግን በሰይፍና በእሳት ነበልባል በምርኮና በመበዝበዝ ብዙ ዘመን ይወድቃሉ።
34 ፤ በወደቁም ጊዜ በጥቂት እርዳታ ይረዳሉ፤ ብዙ ሰዎችም በግብዝነት ወደ እነርሱ ተባብረው ይሰበሰባሉ።
35 ፤ እስከ ተወሰነውም ዘመን ይሆናልና ከጥበበኞቹ አያሌዎቹ እስከ ፍጻሜ ዘመን ይነጥሩና ይጠሩ ይነጡም ዘንድ ይወድቃሉ።
36 ፤ ንጉሡም እንደ ፈቃዱ ያደርጋል፤ ራሱንም ከፍ ከፍ ያደርጋል፥ በአማልክት ሁሉ ላይ ራሱን ታላቅ ያደርጋል፥ በአማልክትም አምላክ ላይ በትዕቢት ይናገራል፤ ቍጣም እስኪፈጸም ድረስ ይከናወንለታል፥ የተወሰነው ይደረጋልና።
37 ፤ የአባቶቹንም አማልክት የሴቶችንም ምኞት አይመለከትም፤ ራሱንም በሁሉ ላይ ታላቅ ያደርጋልና አማልክትን ሁሉ አይመለከትም።
38 ፤ በእነዚህ ፋንታ ግን የአምባዎቹን አምላክ ያከብራል፤ አባቶቹም ያላወቁትን አምላክ በወርቅና በብር በዕንቍና በከበረ ነገር ያከብረዋል።
39 ፤ በእንግዳም አምላክ እርዳታ በጽኑ አምባ ላይ ያደርጋል፤ ለሚያውቁት ክብር ያበዛላቸዋል፥ በብዙም ላይ ያስገዛቸዋል፥ ምድርንም በዋጋ ይከፍላል።
40 ፤ በፍጻሜ ዘመንም የደቡብ ንጉሥ ከእርሱ ጋር ይዋጋል፤ የሰሜንም ንጉሥ ከሰረገሎችና ከፈረሰኞች ከብዙም መርከቦች ጋር እንደ ዐውሎ ነፋስ ይመጣበታል፤ ወደ አገሮችም ይገባል፥ ይጐርፍማል፥ ያልፍማል።
41 ፤ ወደ መልካሚቱም ምድር ይገባል፥ ብዙ አገሮችም ይወድቃሉ፤ ነገር ግን ኤዶምያስና ሞዓብ ከአሞንም ልጆች የበለጡት ከእጁ ይድናሉ።
42 ፤ እጁን በአገሮች ላይ ይዘረጋል፥ የግብጽም ምድር አታመልጥም።
43 ፤ በወርቅና በብርም መዝገብ ላይ፥ በከበረችም በግብጽ ዕቃ ሁሉ ላይ ይሠለጥናል፤ የልብያና የኢትዮጵያ ሰዎችም ይከተሉታል።
44 ፤ ከምሥራቅና ከሰሜን ግን ወሬ ያውከዋል፤ ብዙ ሰዎችንም ይገድል ዘንድና ፈጽሞ ያጠፋ ዘንድ በታላቅ ቍጣ ይወጣል።
45 ፤ ንጉሣዊ ድንኳኑንም በባሕርና በከበረው በቅዱስ ተራራ መካከል ይተክላል፤ ወደ ፍጻሜው ግን ይመጣል፥ ማንም አይረዳውም።