መጽሐፈ ሩት

1 2 3 4


ምዕራፍ 3

አማትዋም ኑኃሚን አለቻት። ልጄ ሆይ፥ መልካም እንዲሆንልሽ ዕረፍት አልፈልግልሽምን?
2 ፤ አሁንም ከገረዶቹ ጋር የነበርሽበት ቦዔዝ ዘመዳችን አይደለምን? እነሆ፥ እርሱ በዛሬ ሌሊት በአውድማው ላይ ገብሱን በመንሽ ይበትናል።
3 ፤ እንግዲህ ታጠቢ፥ ተቀቢ፥ ልብስሽን ተላበሺ፥ ወደ አውድማውም ውረጂ፤ ነገር ግን መብሉንና መጠጡን እስኪጨርስ ድረስ ለሰውዮው አትታዪው።
4 ፤ በተኛም ጊዜ የሚተኛበትን ስፍራ ተመልከቺ፥ ገብተሽም እግሩን ግለጪ፥ ተጋደሚም፤ የምታደርጊውንም እርሱ ይነግርሻል።
5 ፤ ሩትም። የተናገርሽኝን ሁሉ አደርጋለሁ አለቻት።
6 ፤ ወደ አውድማውም ወረደች፥ አማትዋም ያዘዘቻትን ሁሉ አደረገች።
7 ፤ ቦዔዝም ከበላና ከጠጣ ሰውነቱንም ደስ ካሰኘ በኋላ፥ በእህሉ ክምር አጠገብ ሊተኛ ሄደ፤ ሩትም በቀስታ መጣች፥ እግሩንም ገልጣ ተኛች።
8 ፤ መንፈቀ ሌሊትም በሆነ ጊዜ ሰውዮው ደነገጠ፥ ዘወርም አለ፤ እነሆም፥ አንዲት ሴት በእግርጌው ተኝታ ነበረች።
9 ፤ እርሱም። ማን ነሽ? አለ። እርስዋም። እኔ ባሪያህ ሩት ነኝ፤ ዋርሳዬ ነህና ልብስህን በባሪያህ ላይ ዘርጋ አለችው።
10 ፤ ቦዔዝም አላት። ልጄ ሆይ፥ በእግዚአብሔር የተባረክሽ ሁኚ፤ ባለጠጋም ድሀም ብለሽ ጐበዛዝትን አልተከተልሽምና ከፊተኛው ይልቅ በመጨረሻው ጊዜ ቸርነት አድርገሻል።
11 ፤ አሁንም፥ ልጄ ሆይ፥ አትፍሪ፤ በአገሬ ያሉ ሕዝብ ሁሉ ምግባረ መልካም ሴት እንደ ሆንሽ ያውቃሉና ያልሽውን ነገር ሁሉ አደርግልሻለሁ።
12 ፤ የቅርብ ዘመድ መሆኔ እውነት ነው፤ ነገር ግን ከእኔ የቀረበ ዘመድ አለ።
13 ፤ ዛሬ ሌሊት እደሪ፤ ነገም እርሱ ዋርሳ መሆን ቢወድድ መልካም ነው፥ ዋርሳ ይሁን፤ ዋርሳ ሊሆን ባይወድድ ግን፥ ሕያው እግዚአብሔርን እኔ ዋርሳ እሆንሻለሁ፤ እስኪነጋ ድረስ ተኚ።
14 ፤ እስኪነጋም በእግርጌው ተኛች፤ ቦዔዝም። ሴት ወደ አውድማው እንደ መጣች ማንም እንዳያውቅ ብሎ ነበርና ገና ሰውና ሰው ሳይተያይ ተነሣች።
15 ፤ እርሱም። የለበስሽውን ኩታ አምጥተሽ ያዢው አላት፤ በያዘችም ጊዜ ስድስት መስፈሪያ ገብስ ሰፈረላት አሸከማትም።
16 ፤ እርሱም ወደ ከተማይቱ ሄደ። ወደ አማትዋም መጣች፥ አማትዋም። ልጄ ሆይ እንዴት ነሽ? አለቻት፤ እርስዋም ሰውዮው ያደረገላትን ሁሉ ነገረቻት።
17 ፤ ወደ አማትሽ ባዶ እጅሽን አትሂጂ ብሎ ይህን ስድስት መስፈሪያ ገብስ ሰጠኝ አለቻት።
18 ፤ እርስዋም። ልጄ ሆይ፥ ሰውዮው ይህን ነገር ዛሬ እስኪጨርስ ድረስ አያርፍምና ፍጻሜው እስኪታወቅ ድረስ ዝም በዪ አለች።