መጽሐፈ ሩት

1 2 3 4


ምዕራፍ 2

ለኑኃሚንም ባል የሚዘመደው ከአቤሜሌክ ወገን የሆነ ኃያል ሰው ስሙ ቦዔዝ የተባለ ሰው ነበረ።
2 ፤ ሞዓባዊቱም ሩት ኑኃሚንን። በፊቱ ሞገስ የማገኘውን ተከትዬ እህል እንድቃርም ወደ እርሻ ልሂድ አለቻት። እርስዋም። ልጄ ሆይ፥ ሂጂ አለቻት።
3 ፤ ሄደችም፥ ከአጫጆችም በኋኋኋ ላ በእርሻ ውስጥ ቃረ እንደ አጋጣሚውም የአቤሜሌክ ወገን ወደ ነበረው ወደ ቦዔዝ እርሻ ደረሰች።
4 ፤ እነሆም፥ ቦዔዝ ከቤተ ልሔም መጣ፥ አጫጆችንም። እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር ይሁን አላቸው። እነርሱም። እግዚአብሔር ይባርክህ ብለው መለሱለት።
5 ፤ ቦዔዝም በአጫጆች ላይ አዛዥ የነበረውን ሎሌውን። ይህች ቆንጆ የማን ናት? አለው።
6 ፤ የአጫጆቹም አዛዥ። ይህችማ ከሞዓብ ምድር ከኑኃሚን ጋር የመጣች ሞዓባዊቱ ቆንጆ ናት፤
7 ፤ እርስዋም። ከአጫጆቹ በኋላ በነዶው መካከል እንድቃርምና እንድለቅም፥ እባክህ፥ ፍቀድልኝ አለች፤ መጣችም፥ ከማለዳም ጀምራ እስከ አሁን ድረስ ቆይታለች፤ በቤትም ጥቂት ጊዜ እንኳ አላረፈችም አለው።
8 ፤ ቦዔዝም ሩትን። ልጄ ሆይ፥ ትሰሚያለሽን? ቃርሚያ ለመቃረም ወደ ሌላ እርሻ አትሂጂ፥ ከዚህም አትላወሺ፥ ነገር ግን ገረዶቼን ተጠጊ።
9 ፤ ወደሚያጭዱበትም ስፍራ ተመልከቺ፥ ተከተያቸውም፤ እንዳያስቸግሩሽም ጐበዛዝቱን አዝዣለሁ፤ በተጠማሽም ጊዜ ወደ ማድጋው ሄደሽ ጐበዛዝቱ ከቀዱት ውኃ ጠጪ አላት።
10 ፤ በግምባርዋም ተደፍታ በምድር ላይ ሰገደችለት። እኔንስ ለመቀበል በምን ነገር በፊትህ ሞገስ አገኘሁ? እኔ እንግዳ አይደለሁምን? አለችው።
11 ፤ ቦዔዝም። ባልሽ ከሞተ በኋላ አባትሽንና እናትሽን የተወለድሽባትንም ምድር ትተሽ ቀድሞ ወደማታውቂው ሕዝብ እንደ መጣሽ፥ ለአማትሽ ያደረግሽውን ነገር ሁሉ ፈጽሞ ሰምቻለሁ።
12 ፤ እግዚአብሔር እንደ ሥራሽ ይስጥሽ፤ ከክንፉም በታች መጠጊያ እንድታገኚ በመጣሽበት በእስራኤል አምላክ በእግዚአብሔር ዘንድ ደመወዝሽ ፍጹም ይሁን አላት።
13 ፤ እርስዋም። ጌታዬ ሆይ፥ ከባሪያዎችህ እንደ አንዲቱ ሳልሆን አጽናንተኸኛልና፥ የባሪያህንም ልብ ደስ አሰኝተሃልና በዓይንህ ሞገስ ላግኝ አለችው።
14 ፤ በምሳም ጊዜ ቦዔዝ። ወደዚህ ቅረቢ፤ ምሳ ብዪ፥ እንጀራሽንም በሆምጣጤው አጥቅሽ አላት። በአጫጆቹም አጠገብ ተቀመጠች የተጠበሰም እሸት ሰጣት፥ በልታም ጠገበች፥ አተረፈችም።
15 ፤ ደግሞም ልትቃርም በተነሣች ጊዜ ቦዔዝ ጐበዛዝቱን። በነዶው መካከል ትቃርም፥ እናንተም አታሳፍሩአት፤
16 ፤ ደግሞ ከነዶው አስቀርታችሁ ተዉላት፤ እርስዋም ትቃርም፥ አትውቀሱአትም ብሎ አዘዛቸው።
17 ፤ በእርሻውም ውስጥ እስከ ማታ ድረስ ቃረመች፤ የቃረመችውንም ወቃችው፤ አንድ የኢፍ መስፈሪያ ያህልም ገብስ ሆነ።
18 ፤ ተሸክማውም ወደ ከተማ ገባች፥ አማትዋም የቃረመችውን አየች፤ ከጠገበችም በኋላ የተረፋትን አውጥታ ሰጠቻት።
19 ፤ አማትዋም። ዛሬ ወዴት ቃረምሽ? ወዴትስ ሠራሽ? የተቀበለሽ የተባረከ ይሁን አለቻት። እርስዋም። ዛሬ የሠራሁበት ሰው ስም ቦዔዝ ይባላል ብላ በማን ዘንድ እንደ ሠራች ለአማትዋ ነገረቻት።
20 ፤ ኑኃሚንም ምራትዋን። ቸርነቱን በሕያዋንና በሙታን ላይ አልተወምና በእግዚአብሔር የተባረከ ይሁን አለቻት። ኑኃሚንም ደግሞ። ይህ ሰው የቅርብ ዘመዳችን ነው፥ እርሱም ሊቤዡን ከሚችሉት አንዱ ነው አለቻት።
21 ፤ ሞዓባዊቱ ሩትም። ደግሞ። መከሬን እስኪጨርሱ ድረስ ጐበዛዝቴን ተጠጊ አለኝ አለቻት።
22 ፤ ኑኃሚንም ምራትዋን ሩትን። ልጄ ሆይ፥ ከገረዶቹ ጋር ብትወጪ፥ በሌላም እርሻ ባያገኙሽ መልካም ነው አለቻት።
23 ፤ ሩትም የገብሱና የስንዴው መከር እስኪጨረስ ድረስ ልትቃርም የቦዔዝን ገረዶች ተጠጋች፤ በአማትዋም ዘንድ ትቀመጥ ነበር።