1ኛ የዮሐንስ መልእክት
ምዕራፍ 5
ክርስቶስ ነው ብሎ በኢየሱስ የሚያምን ሁሉ ከእግዚአብሔር ተወልዶአል፥ ወላጁንም የሚወድ ሁሉ ከእርሱ የተወለደውን ደግሞ ይወዳል።
2 እግዚአብሔርን ስንወድ ትእዛዛቱንም ስናደርግ የእግዚአብሔርን ልጆች እንድንወድ በዚህ እናውቃለን።
3 ትእዛዛቱን ልንጠብቅ የእግዚአብሔር ፍቅር ይህ ነውና፤ ትእዛዛቱም ከባዶች አይደሉም።
4 ከእግዚአብሔር የተወለደ ሁሉ ዓለምን ያሸንፋልና፤ ዓለምንም የሚያሸንፈው እምነታችን ነው።
5 ኢየሱስም የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ ከሚያምን በቀር ዓለምን የሚያሸንፍ ማን ነው?
6 በውኃና በደም የመጣ ይህ ነው እርሱም ኢየሱስ ክርስቶስ፤ በውኃውና በደሙ እንጂ በውኃው ብቻ አይደለም።
7 መንፈስም እውነት ነውና የሚመሰክረው መንፈስ ነው።
8 የሚመሰክሩት መንፈሱና ውኃው ደሙም ሦስት ናቸውና፤ ሦስቱም በአንድ ይስማማሉ።
9 የሰውን ምስክር ብንቀበል የእግዚአብሔር ምስክር ከእርሱ ይልቅ ይበልጣል፤ ስለ ልጁ የመሰከረው የእግዚአብሔር ምስክር ይህ ነውና።
10 በእግዚአብሔር ልጅ የሚያምን በነፍሱ ምስክር አለው፤ በእግዚአብሔር የማያምን እግዚአብሔር ስለ ልጁ የመሰከረውን ምስክር ስላላመነ ሐሰተኛ አድርጎታል።
11 እግዚአብሔርም የዘላለምን ሕይወት እንደ ሰጠን ይህም ሕይወት በልጁ እንዳለ ምስክሩ ይህ ነው።
12 ልጁ ያለው ሕይወት አለው፤ የእግዚአብሔር ልጅ የሌለው ሕይወት የለውም።
13 የዘላለም ሕይወት እንዳላችሁ ታውቁ ዘንድ በእግዚአብሔር ልጅ ስም ለምታምኑ ይህን ጽፌላችኋለሁ።
14 በእርሱ ዘንድ ያለን ድፍረት ይህ ነው፤ እንደ ፈቃዱ አንዳች ብንለምን ይሰማናል።
15 የምንለምነውንም ሁሉ እንዲሰማልን ብናውቅ ከእርሱ የለመነውን ልመና እንደ ተቀበልን እናውቃለን።
16 ማንም ወንድሙን ሞት የማይገባውን ኃጢአት ሲያደርግ ቢያየው ይለምን፥ ሞትም የማይገባውን ኃጢአት ላደረጉት ሕይወት ይሰጥለታል። ሞት የሚገባው ኃጢአት አለ፤ ስለዚያ እንዲጠይቅ አልልም።
17 ዓመፃ ሁሉ ኃጢአት ነው፥ ሞትም የማይገባው ኃጢአት አለ።
18 ከእግዚአብሔር የተወለደ ሁሉ ኃጢአትን እንዳያደርግ፥ ነገር ግን ከእግዚአብሔር የተወለደው ራሱን እንዲጠብቅ ክፉውም እንዳይነካው እናውቃለን።
19 ከእግዚአብሔር እንደ ሆንን ዓለምም በሞላው በክፉው እንደ ተያዘ እናውቃለን።
20 የእግዚአብሔርም ልጅ እንደ መጣ፥ እውነተኛም የሆነውን እናውቅ ዘንድ ልቡናን እንደ ሰጠን እናውቃለን፤ እውነተኛም በሆነው በእርሱ አለን፥ እርሱም ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። እርሱ እውነተኛ አምላክና የዘላለም ሕይወት ነው።
21 ልጆች ሆይ፥ ከጣዖታት ራሳችሁን ጠብቁ።