የሐዋርያት ሥራ
ምዕራፍ 13
በአንጾኪያም ባለችው ቤተ ክርስቲያን ነቢያትና መምህራን ነበሩ፤ እነርሱም በርናባስ፥ ኔጌር የተባለው ስምዖንም፥ የቀሬናው ሉክዮስም፥ የአራተኛው ክፍል ገዥ የሄሮድስም ባለምዋል ምናሔ፥ ሳውልም ነበሩ።
2 እነዚህም ጌታን ሲያመልኩና ሲጦሙ መንፈስ ቅዱስ። በርናባስንና ሳውልን ለጠራኋቸው ሥራ ለዩልኝ አለ።
3 በዚያን ጊዜም ከጦሙ ከጸለዩም እጃቸውንም ከጫኑ በኋላ አሰናበቱአቸው።
4 እነርሱም በመንፈስ ቅዱስ ተልከው ወደ ሴሌውቅያ ወረዱ፤ ከዚያም በመርከብ ወደ ቆጵሮስ ሄዱ።
5 በስልማናም በነበሩ ጊዜ በአይሁድ ምኵራቦች የእግዚአብሔርን ቃል ሰበኩ፤ አገልጋይም ዮሐንስ ነበራቸው።
6 ደሴቲቱንም ሁሉ እስከ ጳፉ በዞሩ ጊዜ፥ በርያሱስ የሚሉትን ጠንቋይና ሐሰተኛ ነቢይ የሆነውን አንድ አይሁዳዊ ሰው አገኙ፤
7 እርሱም አስተዋይ ሰው ከሆነው ሰርግዮስ ጳውሎስ ከሚባለው አገረ ገዥ ጋር ነበረ። ይህም በርናባስንና ሳውልን ወደ እርሱ ጠርቶ የእግዚአብሔርን ቃል ሊሰማ ፈለገ።
8 ጠንቋዩ ግን ኤልማስ፥ ስሙ እንዲሁ ይተረጐማልና፥ አገረ ገዡን ከማመን ሊያጣምም ፈልጎ ተቃወማቸው።
9 ጳውሎስ የተባለው ሳውል ግን መንፈስ ቅዱስን ተሞልቶ ትኵር ብሎ ሲመለከተው።
10 አንተ ተንኰል ሁሉ ክፋትም ሁሉ የሞላብህ፥ የዲያብሎስ ልጅ፥ የጽድቅም ሁሉ ጠላት፥ የቀናውን የጌታን መንገድ ከማጣመም አታርፍምን?
11 አሁንም፥ እነሆ፥ የጌታ እጅ በአንተ ላይ ናት፥ ዕውርም ትሆናለህ እስከ ጊዜውም ፀሐይን አታይም አለው። ያን ጊዜም ጭጋግና ጨለማ ወደቀበት፥ በእጁም የሚመራውን እየዞረ ፈለገ።
12 በዚያን ጊዜ አገረ ገዡ የተደረገውን ባየ ጊዜ ከጌታ ትምህርት የተነሣ ተገርሞ አመነ።
13 ጳውሎስም ከጓደኞቹ ጋር ከጳፉ ተነሥቶ የጵንፍልያ ወደምትሆን ወደ ጴርጌን መጣ፤ ዮሐንስም ከእነርሱ ተለይቶ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሰ።
14 እነርሱ ግን ከጴርጌን አልፈው የጲስድያ ወደምትሆን ወደ አንጾኪያ ደረሱ፤ በሰንበትም ቀን ወደ ምኵራብ ገብተው ተቀመጡ።
15 ሕግና ነቢያትም ከተነበቡ በኋላ የምኵራቡ አለቆች። ወንድሞች ሆይ፥ ሕዝብን የሚመክር ቃል እንዳላችሁ ተናገሩ ብለው ላኩባቸው።
16 ጳውሎስም ተነሣና በእጁ ጠቅሶ እንዲህ አለ። የእስራኤል ሰዎችና እግዚአብሔርን የምትፈሩት ሆይ፥ ስሙ።
17 የዚህ የእስራኤል ሕዝብ አምላክ አባቶቻችንን መርጦ በግብፅ አገር በእንግድነት ሳሉ ሕዝቡን ከፍ ከፍ አደረጋቸው፥ ከፍ ባለችውም ክንዱ ከዚያ አወጣቸው።
18 በበረሀም አርባ ዓመት ያህል መገባቸው።
19 በከነዓንም አገር ሰባት አሕዛብን አጥፍቶ ምድራቸውን አወረሳቸው።
20 ከዚህም በኋላ እስከ ነቢዩ እስከ ሳሙኤል ድረስ አራት መቶ አምሳ ዓመት ያህል መሳፍንትን ሰጣቸው።
21 ከዚያም ወዲያ ንጉሥን ያነግሥላቸው ዘንድ ለመኑ፥ እግዚአብሔርም ከብንያም ወገን የሚሆን ሰው የቂስን ልጅ ሳኦልን አርባ ዓመት ሰጣቸው፤
22 እርሱንም ከሻረው በኋላ ዳዊትን በእነርሱ ላይ እንዲነግሥ አስነሣው፥ ሲመሰክርለትም። እንደ ልቤ የሆነ ሰው ፈቃዴንም ሁሉ የሚያደርግ የእሴይን ልጅ ዳዊትን አገኘሁ አለ።
23 ከዚህም ሰው ዘር እግዚአብሔር እንደ ተስፋው ቃል ለእስራኤል መድኃኒትን እርሱም ኢየሱስን አመጣ።
24 ከመምጣቱ በፊት ዮሐንስ አስቀድሞ ለእስራኤል ሕዝብ ሁሉ የንስሐን ጥምቀት ሰብኮ ነበር።
25 ዮሐንስም ሩጫውን ሲፈጽም ሳለ። እኔ ማን እንደ ሆንሁ ታስባላችሁ? እኔስ እርሱን አይደለሁም፤ ነገር ግን እነሆ፥ የእግሩን ጫማ እፈታ ዘንድ ከማይገባኝ ከእኔ በኋላ ይመጣል ይል ነበር።
26 እናንተ ወንድሞቻችን፥ የአብርሃም ዘር ልጆች ከእናንተ መካከልም እግዚአብሔርን የምትፈሩ ሆይ፥ ለእናንተ የዚህ የመዳን ቃል ተላከ።
27 በኢየሩሳሌም የሚኖሩ ሰዎችና አለቆቻቸው እርሱንና በየሰንበቱ የሚነበቡትን የነቢያትን ድምፆች ስላላወቁ በፍርዳቸው ፈጽመዋልና፤
28 ለሞትም የሚያደርስ ምክንያት አንድ ስንኳ ባያገኙበት፥ ይገድለው ዘንድ ጲላጦስን ለመኑት፤
29 ስለ እርሱም የተጻፈውን ሁሉ በፈጸሙ ጊዜ ከእንጨት አውርደው በመቃብር አኖሩት።
30 እግዚአብሔር ግን ከሙታን አስነሣው፤
31 በሕዝብም ዘንድ ምስክሮቹ ለሆኑት ከእርሱ ጋር ከገሊላ ወደ ኢየሩሳሌም ለወጡት ብዙ ቀን ታያቸው።
32 እኛም ለአባቶች የተሰጠውን ተስፋ የምስራቹን ለእናንተ እንሰብካለን፤
33 ይህን ተስፋ እግዚአብሔር በሁለተኛው መዝሙር ደግሞ። አንተ ልጄ ነህ እኔ ዛሬ ወለድሁህ ተብሎ እንደ ተጻፈ፥ ኢየሱስን አስነሥቶ ለእኛ ለልጆቻቸው ፈጽሞአልና።
34 እንደገናም ወደ መበስበስ እንዳይመለስ ከሙታን እንደ አስነሣው፥ እንዲህ። የታመነውን የዳዊትን ቅዱስ ተስፋ እሰጣችኋለሁ ብሎአል።
35 ደግሞ በሌላ ስፍራ። ቅዱስህን መበስበስን ያይ ዘንድ አትሰጠውም ይላልና።
36 ዳዊትም በራሱ ዘመን የእግዚአብሔርን አሳብ ካገለገለ በኋላ አንቀላፋ፥ ከአባቶቹም ጋር ተጨምሮ መበስበስን አየ፤
37 ይህ እግዚአብሔር ያስነሣው ግን መበስበስን አላየም።
38 -
39 እንግዲህ ወንድሞች ሆይ፥ በእርሱ በኩል የኃጢአት ስርየት እንዲነገርላችሁ፥ በሙሴም ሕግ ትጸድቁበት ዘንድ ከማይቻላችሁ ሁሉ ያመነ ሁሉ በእርሱ እንዲጸድቅ በእናንተ ዘንድ የታወቀ ይሁን።
40 -
41 እንግዲህ። እናንተ የምትንቁ፥ እዩ ተደነቁም ጥፉም አንድ ስንኳ ቢተርክላችሁ የማታምኑትን ሥራ በዘመናችሁ እኔ እሠራለሁና ተብሎ በነቢያት የተነገረው እንዳይደርስባችሁ ተጠንቀቁ።
42 በወጡም ጊዜ ይህን ነገር በሚመጣው ሰንበት ይነግሩአቸው ዘንድ ለመኑአቸው።
43 ጉባኤውም ከተፈታ በኋላ ከአይሁድና ወደ ይሁዲነት ገብተው ከሚያመልኩ ብዙዎች ጳውሎስንና በርናባስን ተከተሉአቸው፥ እነርሱም ሲነግሩአቸው በእግዚአብሔር ጸጋ ጸንተው እንዲኖሩ አስረዱአቸው።
44 በሁለተኛውም ሰንበት ከጥቂቶቹ በቀር የከተማው ሰው ሁሉ የእግዚአብሔርን ቃል ይሰሙ ዘንድ ተሰበሰቡ።
45 አይሁድም ብዙ ሕዝብ ባዩ ጊዜ ቅንዓት ሞላባቸው፥ እየተሳደቡም ጳውሎስ የተናገረውን ቃል ተቃወሙ።
46 ጳውሎስና በርናባስም ገልጠው። የእግዚአብሔር ቃል አስቀድሞ ለእናንተ ይነገር ዘንድ ያስፈልጋል፤ ከገፋችሁትና የዘላለም ሕይወት እንዳይገባችሁ በራሳችሁ ከፈረዳችሁ ግን፥ እነሆ፥ ወደ አሕዛብ ዘወር እንላለን።
47 እንዲሁ ጌታ። እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ለማዳን ትሆን ዘንድ ለአሕዛብ ብርሃን አድርጌሃለሁ ብሎ አዞናልና አሉ።
48 አሕዛብም ሰምተው ደስ አላቸው የእግዚአብሔርንም ቃል አከበሩ፥ ለዘላለም ሕይወትም የተዘጋጁ ሁሉ አመኑ፤
49 የጌታም ቃል በአገሩ ሁሉ ተስፋፋ።
50 አይሁድ ግን የሚያመልኩትን የከበሩትንም ሴቶችና የከተማውን መኳንንት አወኩ፥ በጳውሎስና በበርናባስም ላይ ስደትን አስነሥተው ከአገራቸው አወጡአቸው።
51 እነርሱ ግን የእግራቸውን ትቢያ አራግፈውባቸው ወደ ኢቆንዮን መጡ።
52 በደቀ መዛሙርትም ደስታና መንፈስ ቅዱስ ሞላባቸው።