ምዕራፍ 21

ከዚህ በኋላ ኢየሱስ በጥብርያዶስ ባሕር አጠገብ ለደቀ መዛሙርቱ እንደ ገና ተገለጠላቸው፤
2 እንዲህም ተገለጠ። ስምዖን ጴጥሮስና ዲዲሞስ የሚባለው ቶማስ ከገሊላ ቃና የሆነ ናትናኤልም የዘብዴዎስም ልጆች ከደቀ መዛሙርቱም ሌሎች ሁለት በአንድነት ነበሩ።
3 ስምዖን ጴጥሮስ። ዓሣ ላጠምድ እሄዳለሁ አላቸው። እነርሱም። እኛም ከአንተ ጋር እንመጣለን አሉት። ወጥተውም ወደ ታንኳይቱ ገቡ በዚያችም ሌሊት ምንም እላጠመዱም።
4 በነጋም ጊዜ ኢየሱስ በባሕር ዳር ቆመ፤ ደቀ መዛሙርቱ ግን ኢየሱስ መሆኑን አላወቁም።
5 ኢየሱስም። ልጆች ሆይ፥ አንዳች የሚበላ አላችሁን? አላቸው። የለንም ብለው መለሱለት።
6 እርሱም። መረቡን በታንኳይቱ በስተ ቀኝ ጣሉት ታገኙማላችሁ አላቸው። ስለዚህ ጣሉት፤ በዚህም ጊዜ ከዓሣው ብዛት የተነሣ ሊጐትቱት አቃታቸው።
7 ኢየሱስ ይወደው የነበረውም ደቀ መዝሙር ጴጥሮስን። ጌታ እኮ ነው አለው። ስለዚህ ስምዖን ጴጥሮስ ጌታ መሆኑን በሰማ ጊዜ ዕራቁቱን ነበረና ልብሱን ታጥቆ ወደ ባሕር ራሱን ጣለ።
8 ሌሎቹ ደቀ መዛሙርት ግን ከምድር ሁለት መቶ ክንድ ያህል እንጂ እጅግ አልራቁም ነበርና ዓሣ የሞላውን መረብ እየሳቡ በጀልባ መጡ።
9 ወደ ምድርም በወጡ ጊዜ ፍምና ዓሣ በላዩ ተቀምጦ እንጀራም አዩ።
10 ኢየሱስም። አሁን ካጠመዳችሁት ዓሣ አምጡ አላቸው።
11 ስምዖን ጴጥሮስም ወደ ጀልባይቱ ገብቶ መቶ አምሳ ሦስት ታላላቅ ዓሦች ሞልቶ የነበረውን መረብ ወደ ምድር ጐተተ፤ ይህንም ያህል ብዙ ሲሆን መረቡ አልተቀደደም።
12 ኢየሱስም። ኑ፥ ምሳ ብሉ አላቸው። ከደቀ መዛሙርቱ አንድ ስንኳ። አንተ ማን ነህ? ብሎ ሊመረምረው የደፈረ አልነበረም፤ ጌታ መሆኑን አውቀው ነበርና።
13 ኢየሱስም መጣና እንጀራ አንሥቶ ሰጣቸው፥ እንዲሁም ዓሣውን።
14 ኢየሱስ ከሙታን ከተነሣ በኋላ ለደቀ መዛሙርቱ ሲገለጥላቸው ይህ ሦስተኛው ጊዜ ነበረ።
15 ምሳ ከበሉ በኋላም ኢየሱስ ስምዖን ጴጥሮስን። የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፥ ከእነዚህ ይልቅ ትወደኛለህን? አለው። አዎን ጌታ ሆይ፥ እንድወድህ አንተ ታውቃለህ አለው። ግልገሎቼን አሰማራ አለው።
16 ደግሞ ሁለተኛ። የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፥ ትወደኛለህን? አለው። አዎን ጌታ ሆይ፥ እንድወድህ አንተ ታውቃለህ አለው።
17 ጠቦቶቼን ጠብቅ አለው። ሦስተኛ ጊዜ። የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፥ ትወደኛለህን? አለው። ሦስተኛ። ትወደኛለህን? ስላለው ጴጥሮስ አዘነና። ጌታ ሆይ፥ አንተ ሁሉን ታውቃለህ፤ እንድወድህ አንተ ታውቃለህ አለው። ኢየሱስም። በጎቼን አሰማራ።
18 እውነት እውነት እልሃለሁ፥ አንተ ጐልማሳ ሳለህ ወገብህን በገዛ ራስህ ታጥቀህ ወደምትወደው ትሄድ ነበር፤ ነገር ግን በሸመገልህ ጊዜ እጆችህን ትዘረጋለህ፥ ሌላውም ያስታጥቅሃል ወደማትወደውም ይወስድሃል አለው።
19 በምን ዓይነት ሞት እግዚአብሔርን ያከብር ዘንድ እንዳለው ሲያመለክት ይህን አለ። ይህንም ብሎ። ተከተለኝ አለው።
20 ጴጥሮስም ዘወር ብሎ ኢየሱስ ይወደው የነበረውን ደቀ መዝሙር ሲከተለው አየ፤ እርሱም ደግሞ በእራት ጊዜ በደረቱ ተጠግቶ። ጌታ ሆይ፥ አሳልፎ የሚሰጥህ ማን ነው? ያለው ነበረ።
21 ጴጥሮስም ይህን አይቶ ኢየሱስን። ጌታ ሆይ፥ ይህስ እንዴት ይሆናል? አለው።
22 ኢየሱስም። እስክመጣ ድረስ ይኖር ዘንድ ብወድስ፥ ምን አግዶህ? አንተ ተከተለኝ አለው።
23 ስለዚህ። ያ ደቀ መዝሙር አይሞትም የሚለው ይህ ነገር ወደ ወንድሞች ወጣ፤ ነገር ግን ኢየሱስ። እስክመጣ ድረስ ይኖር ዘንድ ብወድስ ምን አግዶህ? አለው እንጂ አይሞትም አላለውም።
24 ስለ እነዚህም የመሰከረ ይህንንም ጽፎ ያለ ይህ ደቀ መዝሙር ነው፥ ምስክሩም እውነት እንደ ሆነ እናውቃለን።
25 ኢየሱስም ያደረገው ብዙ ሌላ ነገር ደግሞ አለ፤ ሁሉ በእያንዳንዱ ቢጻፍ ለተጻፉት መጻሕፍት ዓለም ራሱ ባልበቃቸውም ይመስለኛል።