ትንቢተ ሐጌ
ምዕራፍ 2
በሰባተኛው ወር ከወሩም በሀያ አንደኛው ቀን የእግዚአብሔር ቃል በነቢዩ በሐጌ እጅ እንዲህ ሲል መጣ።
2 ፤ ለይሁዳ አለቃ ለሰላትያል ልጅ ለዘሩባቤል፥ ለታላቁም ካህን ለኢዮሴዴቅ ልጅ ለኢያሱ፥ ለቀሩትም ሕዝብ እንዲህ ስትል ተናገር።
3 ፤ በቀድሞ ክብሩ ሳለ ይህን ቤት ያየ በእናንተ መካከል የቀረ ማን ነው? ዛሬስ እንዴት ሆኖ አያችሁት? በዓይናችሁ እንደ ምናምን አይደለምን?
4 ፤ አሁን ግን፥ ዘሩባቤል ሆይ፥ በርታ፥ ይላል እግዚአብሔር፤ ታላቁም ካህን የኢዮሴዴቅ ልጅ ኢያሱ ሆይ፥ በርታ፥ እናንተም የአገሩ ሕዝብ ሆይ፥ በርቱና ሥሩ፥ ይላል እግዚአብሔር፤ እኔ ከእናንተ ጋር ነኝና፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር።
5 ፤ መንፈሴም በመካከላችሁ ይኖራልና አትፍሩ።
6 ፤ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና። ገና አንድ ጊዜ በቅርብ ዘመን እኔ ሰማያትንና ምድርን ባሕርንና የብስንም አናውጣለሁ፤
7 ፤ አሕዛብን ሁሉ አናውጣለሁ፥ በአሕዛብ ሁሉ የተመረጠውም ዕቃ ይመጣል፤ ይህንም ቤት በክብር እሞላዋለሁ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር።
8 ፤ ብሩ የእኔ ነው፥ ወርቁም የእኔ ነው፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር።
9 ፤ ከፊተኛው ይልቅ የዚህ የሁለተኛው ቤት ክብር ይበልጣል፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፤ በዚህም ስፍራ ሰላምን እሰጣለሁ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር።
10 ፤ በዳርዮስም በሁለተኛው ዓመት በዘጠነኛው ወር በሀያ አራተኛው ቀን የእግዚአብሔር ቃል በነቢዩ በሐጌ እጅ እንዲህ ሲል መጣ።
11 ፤ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ካህናቱን ስለ ሕጉ ጠይቅ፤
12 ፤ አንድ ሰው የተቀደሰ ሥጋ በልብሱ ዘርፍ ቢይዝ፥ በዘርፉም እንጀራ ወይም ወጥ፥ ወይም የወይን ጠጅ፥ ወይም ዘይት፥ ወይም ማናቸውም መብል ቢነካ ያ የተነካው በውኑ ይቀደሳልን? ብለህ ካህናቱን ጠይቃቸው፤ ካህናቱም። አይሆንም ብለው መለሱ።
13 ፤ ሐጌም። በሬሳ የረከሰ ሰው ከእነዚህ አንዱን ቢነካ ያ የተነካው በውኑ ይረክሳልን? አለ። ካህናቱም። አዎን ይረክሳል ብለው መለሱ።
14 ፤ ሐጌም መልሶ እንዲህ አለ። ይህ ሕዝብና ይህ ወገን በፊቴ እንዲሁ ነው፥ ይላል እግዚአብሔር፤ የእጃቸውም ሥራ ሁሉ እንዲሁ ነው፤ በዚያም ያቀረቡት ነገር ርኩስ ነው።
15 ፤ አሁንም ድንጋይ በድንጋይ ላይ በእግዚአብሔር መቅደስ ሳይነባበር፥ ከዛሬ ጀምራችሁ ወዳለፈው ዘመን ልብ አድርጉ።
16 ፤ በዚያን ዘመን ሁሉ ሰው ሀያ መስፈሪያ ወዳለበት ምርት በመጣ ጊዜ፥ የተገኘው አሥር መስፈሪያ ብቻ ነው፤ አምሳ ማድጋም ይቀዳ ዘንድ ወደ መጥመቂያው በመጣ ጊዜ፥ የተገኘው ሀያ ብቻ ነው።
17 ፤ በእጃችሁ ሥራ ሁሉ ላይ በዋግና በአረማሞ በበረዶም መታኋችሁ፤ እናንተ ግን ወደ እኔ አልተመለሳችሁም፥ ይላል እግዚአብሔር።
18 ፤ ከዛሬው ከዘጠነኛው ወር ከሀያ አራተኛው ቀን ጀምራችሁ የሚመጣውን ዘመን ልብ አድርጉ፤ የእግዚአብሔር መቅደስ መሠረት ከተተከለበት ቀን ጀምሮ ልብ አድርጉ።
19 ፤ ዘር በጎተራ ገና ይኖራልን? ወይንና በለስ ሮማንና ወይራ አላፈሩም፤ ከዚህች ቀን ጀምሬ እባርካችኋለሁ።
20 ፤ በወሩ በሀያ አራተኛው ቀን የእግዚአብሔር ቃል ሁለተኛ ወደ ሐጌ እንዲህ ሲል መጣ።
21 ፤ ለይሁዳ አለቃ ለዘሩባቤል ተናገር እንዲህም በል። ሰማያትንና ምድርን አናውጣለሁ፤
22 ፤ የመንግሥታትንም ዙፋን እገለብጣለሁ፥ የአሕዛብንም መንግሥታት ኃይል አጠፋለሁ፤ ሰረገሎችንና የሚቀመጡባቸውንም እገለብጣለሁ፤ ፈረሶችና ፈረሰኞቻቸውም እያንዳንዳቸው በወንድማቸው ሰይፍ ይወድቃሉ።
23 ፤ ባሪያዬ የሰላትያል ልጅ ዘሩባቤል ሆይ፥ በዚያ ቀን እወስድሃለሁ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፤ እኔ መርጬሃለሁና፥ ይላል እግዚአብሔር፥ እንደ ቀለበት ማተሚያ አደርግሃለሁ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር።