ትንቢተ ናሆም

1 2 3


ምዕራፍ 3

ለደም ከተማ ወዮላት! በሁለንተናዋ ሐሰትና ቅሚያ ሞልቶባታል፤ ንጥቂያ ከእርስዋ አያልቅም።
2 ፤ የአለንጋ ድምፅ፥ የመንኰራኵርም ድምፅ፥ የፈረሶችም ኮቴ፥ የፈጣን ሰረገላም ጩኸት ተሰምቶአል፤
3 ፤ ፈረሰኛው ይጋልባል፥ ሰይፍም ይንቦገቦጋል፥ ጦርም ይብለጨለጫል፤ የተገደሉትም ይበዛሉ፥ በድኖችም በክምር ይከመራሉ፥ ሬሳቸውም አይቈጠርም፤ በሬሳቸውም ይሰናከላሉ።
4 ፤ ስለ ተዋበችው ጋለሞታ ግልሙትና ብዛት ይህ ሆኖአል፤ እርስዋም በመተትዋ እጅግ በለጠች፥ አሕዛብንም በግልሙትናዋ፥ ወገኖችንም በመተትዋ ሸጠች።
5 ፤ እነሆ፥ በአንቺ ላይ ነኝ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፥ ልብስሽን በፊትሽ እገልጣለሁ፤ ኅፍረተ ሥጋሽንም ለአሕዛብ፥ ነውርሽንም ለመንግሥታት አሳያለሁ።
6 ፤ ርኵሰትንም በላይሽ እጥላለሁ፥ እንቅሻማለሁ፥ ማላገጫም አደርግሻለሁ።
7 ፤ የሚያይሽም ሁሉ ከአንቺ ሸሽቶ። ነነዌ ባድማ ሆናለች፤ የሚያለቅስላትስ ማን ነው? የሚያጽናናትንስ ከወዴት እፈልጋለሁ? ይላል።
8 ፤ አንቺ በመስኖች መካከል ከተቀመጠችው፥ ውኃም በዙሪያዋ ከነበራት፥ ምሽግዋም ባሕር ከነበረ፥ ቅጥርዋም በባሕር ውስጥ ከነበረ ከኖእ አሞን ትበልጫለሽን?
9 ፤ ኢትዮጵያና ግብጽ የማይቈጠር ኃይልዋ ነበሩ፤ ፉጥና ልብያ ረዳቶችዋ ነበሩ።
10 ፤ እርስዋ ግን ተማርካ ፈለሰች፤ ሕፃናቶችዋ በመንገድ ሁሉ ራስ ላይ ተፈጠፈጡ፤ በከበርቴዎችዋም ላይ ዕጣ ተጣጣሉ፥ ታላላቆችዋም ሁሉ በሰንሰለት ታሰሩ።
11 ፤ አንቺም ትሰክሪአለሽ ወራዳም ትሆኛለሽ፤ አንቺ ደግሞ ከጠላት የተነሣ መጠጊያን ትፈልጊአለሽ።
12 ፤ አምባሽ ሁሉ የመጀመሪያውን የበሰለ ፍሬ እንደ ያዙ እንደ በለስ ዛፎች ነው፤ ቢወዛወዝ በሚበላው አፍ ውስጥ ይወድቃል።
13 ፤ እነሆ፥ በመካከልሽ ያሉ ሕዝብሽ ሴቶች ናቸው፤ የአገርሽ በሮች ለጠላቶችሽ ፈጽሞ ተከፍተዋል፥ እሳትም መወርወሪያዎችህን በልቶአል።
14 ፤ ከብበው ያስጨንቁሻልና ውኃን ቅጂ፤ አምባሽን አጠንክሪ፤ ወደ ጭቃ ገብተሽ እርገጪ፤ የጡብን መሠሪያ ያዢ።
15 ፤ በዚያ እሳት ይበላሻል፥ ሰይፍ ያጠፋሻል፥ እንደ ደጎብያ ይበላሻል፤ እንደ ደጎብያ ብዢ፥ እንደ አንበጣም ተባዢ።
16 ፤ ነጋዴዎችሽን ከሰማይ ከዋክብት ይልቅ አበዛሽ፤ ደጎብያ ተዘረጋ፥ በረረም።
17 ፤ በአንቺ ዘንድ ዘውድ የጫኑት እንደ አንበጣ፥ አለቆችሽም እንደሚንቀሳቀሱ ኩብኩባዎች ናቸው፤ በብርድ ቀን በቅጥር ውስጥ ይቀመጣሉ፥ ፀሐይም በወጣች ጊዜ ያኰበኵባሉ፤ ስፍራቸው በየት እንደ ሆነ አይታወቅም።
18 ፤ የአሦር ንጉሥ ሆይ፥ እረኞችህ አንቀላፍተዋል፤ መኳንንቶችህም ዐርፈዋል፤ ሕዝብህም በተራሮች ላይ ተበትኖአል፥ የሚሰበስበውም የለም።
19 ፤ ስብራትህ አይፈወስም፥ ቍስልህም ክፉ ነው፤ ወሬህንም የሚሰሙ ሁሉ እጃቸውን በአንተ ላይ ያጨበጭባሉ፤ ክፋትህ ሁልጊዜ ያላለፈችበት ሰው ማን ነውና?